ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትና ዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬቶች መመዝገባቸውን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ተናገሩ።
资产发布器
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በበጀት ዓመቱ የተሰጠውን ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ተልዕኮ ከማሳካት አኳያ ተጨባጭ የሆኑ ስኬቶች መመዝገባቸውን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት እና የአስተዳደሩ የቀጣይ ስትራቴጂ መነሻ ዕቅድ ላይ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ በተገኘበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የዲጂታላይዜሽን ጉዞን ከማሳለጥና ደህንንቱን ከማረጋገጥ አኳያ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ለአብነትም “ቁልፍ የሕዝብ መሰረተ ልማት (Public Key Infrastructure - PKI)” ፣ እና የዲጅታል ፎረንሲክ እና የሳይበር ወንጀል ምርመራ ላብራቶሪ በበጀት አመቱ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸዉን በማሳያነት አንስተዋል።
የሳይበር ጥቃትን የመከላከል አቅምን ከማሳደግ አኳያ በበጀት አመቱ ከፍተኛ እድገት የታየ ሲሆን በ2017 በጀት አመት አስራ ሦስት ሺህ አራት መቶ ዘጠና አራት (13,494) የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መክሸፋቸዉን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ዲጂታይዜሽን ላይ ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ሰፊ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ትዕግስት በበጀት ዓመቱ ለ410 ተቋማት በሚጠቀሟቸዉ ሲስተሞች፣ መሰረተ-ልማቶች እና መተግበሪያዎች ላይ የሳይበር ደህንነት ኦዲት በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገር ፍራውድ እና ዲጂታል ፎረንሲክ ምርመራ ጋር በተያያዘ ለ6,193 ኬዞች ምላሽ የመስጠት ስራ መሰራቱን የጠቆሙት ወ/ሮ ትዕግስት ወደ ሀገር ከሚገቡት የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ላይ የሴኪዩሪቲ ክሊራንስ እንዲሰራ ከተጠየቁ 5,037 ጥያቄዎች መካከል ለ4,925 ምላሽ መሰጠቱንና 112 የሚሆኑት ወደ ሀገር ዉስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ፤ ሀገራዊ የዲጂታላይዜሽን ጉዞን በማሳለጥና ደህንነቱን በማረጋገጥ፤ የሀገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን ከሌሎች የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በመስራት ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል።
አስተዳደሩ በ2017 በጀት አመት ያስመዘገበውን ስኬትና ጥንካሬዎች በማላቅ፤ በ2018 በጀት አመትም ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነትን በተሟላ መልኩ በማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል፡፡