Untitled Basic Web Content

ግዙፍ ዳታ (Big Data)

 

ተለያዩ ተቋማት እና ምሁራን ግዙፍ ዳታን በተለያየ መንገድ ይተረጉሙታል። ለምሳሌ አለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረት (ITU) ግዙፍ ዳታ ጥቅል ስም ሆኖ ውስብስብ ነገሮችን ለመፍታት የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂያዊ አቅሞች የሚገልጽ እና ከተለመደው ዳታ ጋር ሲነጻጸር መጠኑ፣ ፍጥነቱ እና አይነቱ ከፍተኛ የሆነ ዳታ  ነው በማለት ይተረጉመዋል። ግሎባል  ፐልስ የተባለ ሌላው የተባበሩት መንግስታት ተቋም ደግሞ ግዙፍ ዳታ የተደራጀ እና ያልተደራጀ የዳታ መጠንን ለመግለጽ የምንጠቀመው ሀረግ ሲሆን ዳታው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በተለመዱ የመረጃ ቋቶችና የሶፍትዌር ቴክኒኮች ማቀናበር አስቸጋሪ ነው በማለት ይገልጸዋል። የአሜሪካው ብሄራዊ የሳይንስ ፋውንዴሽን ደግሞ ቢግ ዳታን ትልቅ፣ መጠነ ሰፊ እና ውስብስብ ሆነው ከተለያዩ መሳሪያዎች፣ ለይዎች፣ የኢንተርኔት ልውውጦች፣ -ሜይል፣ ቪድዮ፣ ጠቅታዎች (clicks) እና ሌሎች ዲጂታል ምንጮች በአሁኑ ሰአት የሚገኙ እና ለወደፊቱም የሚገኝ የዳታ ስብስብ ነው በማለት ይተረጉመዋል። የጋርትነር ተቋምም የራሱ የሆነ የግዙፍ ዳታ ትርጓሜ አስቀምጧል። በተቋሙ ትርጓሜ መሰረት ግዙፍ ዳታ ከፍተኛ መጠን፣ ከፍተኛ ፍጥነትና የተለያየ አይነት መረጃ የያዘ ጥሪት ሆኖ በአነስተኛ ወጪ እና አዳዲስ መንገዶች መረጃን ማቀናበር የሚያስችልና የተሻለ ትኩረትን፣ ውሳኔ አሰጣጥንና አውቶሜት የማድረግ ሂደትን የሚጠይቅ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ግዙፍ ዳታ መጠኑ እጅግ ሰፊ እና ውስብስብ እንዲሁም በተበታተነ ወይም በተደራጀ መልኩ የሚገኝ የዳታ አይነት ሲሆን ለማቀናበር እና ለመተንተን ለየት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም መሆኑን መረዳት ይቻላል።

  • የግዙፍ ዳታ ምንጮች

ግዙፍ ዳታ በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ምንጮቹም በነዚህ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ግሎባል ፐልስ አራት ምንጮችን ዘርዝሯል። የመጀመሪያው ሰዎች የሚጠቀሙበት የዲጂታል መሳሪያ  ሲሆን ተንቀሳቃሽ ስልኮችን፣ ድር ላይ የሚደረግ ፍለጋ ወዘተ ያጠቃልላል። ሁለተኛው ምንጭ የኦንላይን ኢንፎርሜሽን ነው። ይህ ምንጭ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚደረጉ ግንኙነቶችን፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድን እና የስራ ማስታወቂያዎችን ያካትታል። ሶስተኛው ምንጭ ከአካላዊ ሴንሰሮች የሚሰበሰብ ዳታ ነው። ይህ ምንጭ ከሳተላይት ወይም ከኢንፍራሬድ የሚገኙ የመልክዓ-ምድር፣ የትራፊክ አካሄድ፣ የብርሃን ልቀት፣ የከተማ ልማት፣ ወዘተለውጦች የያዙ ምስሎችን ያጠቃልላል። አራተኛው ምንጭ ዜጎች የሚያቀርቡት መረጃ ሲሆን በተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት ለሚቀርቡ የዳሰሳ ጥናት ጥያቄዎች የሚሰጡ መልሶችን ያጠቃልላል። ዓለምአቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረት አስተዳደራዊ ምንጮች፣ የንግድ ልውውጦች ለይዎችና የክትትል መሳሪያዎች እንዲሁም የኦንላይን ተግባራት ዋና የግዙፍ ዳታ ምንጮች እንደሆኑ ገልጿል።

የግዙፍ ዳታ ጠቀሜታዎች በአግባቡ የተሰበሰበ፣ የተደራጀ፣ የተከማቸ እና ለትንተና ዝግጁ የሆነ መረጃ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰአት የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉ በመሆኑ ከነዚህ መሳሪያዎች የሚመነጭ ዳታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ግዙፍ ዳታ ለልማት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በኦንላይን የሚወጡ የስራ ማስታወቂያዎች የስታቲስቲክስ ባለስልጣን የሚሰበስባቸውን የሰው ሃይል ዳታዎች በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው። ግዙፍ ዳታ የሸቀጦች ወይም የአገልግሎቶች እለታዊ  የዋጋ አዝማሚያ ለማወቅም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ለምሳሌ፡- የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም (MIT) ከኦንላይን ቸርቻሪዎች የዋጋን ተመን የሚሰበስብበት ቢልየን ዋጋ ፕሮጀክት” ( Billion Price Project) ያለው ሲሆን ተመራማሪዎች ከዋጋ                       

የዋጋ ንረት እና የጥሪት ዋጋ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ የማክሮ ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ለመረዳት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። እነዚህ ዳታዎች ከተለመደው ስታቲስቲክስ የሚለዩት በየቀኑ የሚመዘገቡ መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው በአብዛኞቹ ሀገራት የማክሮ ኢኮኖሚ ስታቲስቲክሶች የሚወጡት በየወሩ ቢሆንም  ግዙፍ ዳታ በየቀኑ የሚኖር የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንድናውቅ ይረዳናል። ይህ ደግሞ ወቅታዊ የፖሊሲ ውሳኔ ለማሳለፍ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል።  ግዙፍ ዳታ ምርታማነት በማሳደግ ረገድም የማይናቅ አስተዋጽኦ አለው። የአለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረት  ሪፖርት እንደሚያሳየው ያላቸውን መረጃ በተገቢው መንገድ ለውሳኔ ግብአትነት የተጠቀሙ ተቋማት መረጃን በውሳኔ ግብአትነት ካልተጠቀሙ ተቋማት ምርታማነታቸው በስድስት እጥፍ በልጠው ተገኝተዋል። የግዙፍ ዳታ ተጠቃሚ ከሆኑ አለምአቀፍ ተቋማት አንዱ የተባበሩት መንግስታት ነው። ተቋሙ ኤን ግሎባል ፐልስ( UN Global Pulse)  የተባለ ጅማሮ( initiative)  ያለው ሲሆን ግዙፍ ዳታን ለዘላቂ ልማትና ሰብአዊ ተግባራት ለማዋል ይጠቀምበታል። የአንድ ሀገር ዜጎች በትዊተር እና መሰል ሚድያዎች በስፋት የሚወያዩባቸው ርእሰ ጉዳዮችን በመከታተል ሪፖርቶች ያወጣል። ለምሳሌ ተመድ ይህንን ስርአት በመጠቀም በኢንዶኔዥያ ባለው የትዊተር አጠቃቀም ላይ ክትትል ያደረገ ሲሆን ዓላማው በሀገሪቱ የነበረውን የምግብ ዋጋ ቀውስ ለመረዳት ነበር። ጅማሮው ከምግብ ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ትዊተር ላይ የተቀመጡ ጽሆፎችን (ትዊቶችን) በመለየት የየቀኑ የምግብ ዋጋ አመላካች አዝማሚያ የለየ ሲሆን ከትዊተር ዳታ በመነሳት  የብዙ ሳምንታትን የሸማቾች የዋጋ አመላካች አስቀድሞ መተንበይ ችሏል። ይህ ጅማሮ በተለያዩ ሀገራት ሊኖሩ ስለሚችሉ ድህረ 2015 የልማት አጀንዳዎች ለመረዳትና ለማነጻጸር የትዊተር ዳታን በመጠቀም ላይ ይገኛል። የቴሌኮም አንቀሳቃሾችም ግዙፍ ዳታን የደንበኞቻቸው ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም ይጠቀሙበታል። በተለይ የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማወቅ፣ የደንበኞቻቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቋም ለማወቅ፣ ደንበኞቻቸው በመረቡ እና ከመረቡ ውጭ ያላቸውን ተጽእኖ ለመለካት እንዲሁም የደንበኞቻቸውን ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለማወቅ ይጠቀሙበታል።

አንቀሳቃሾች የመረብ አሰራራቸውን ለማቀድና ለማስተዳደር ግዙፍ ዳታን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ የሁል ጊዜ ተጠቃሚ ደንበኞቻቸውን  እና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ክልሎችን የጂኦስፓሻል መረጃ በመጠቀም አንቀሳቃሾች ሀብቶቻቸውን ወደነዚህ ክልሎችና ደንበኞች መመደብ ይችላሉ። አዳዲስ የቢዝነስ አገልግሎቶች ለመስጠትም ጥቅም ላይ ያውሉታል። አንቀሳቃሾች ዳታውን ለሶስተኛ ወገን በመሸጥም ተጠቃሚ ይሆናሉ። የግዙፍ ዳታን በመጠቀም የሚገኝ የደንበኞች ሁኔታ አዳዲስ የቢዝነስ አይነቶች ለመፍጠርም ጠቃሚ ነው። ለምስሌ ሲግኒፋይ (Cignifi) የተባለ መሰረቱ አሜሪካ ያደረገ የግዙፍ ዳታ ጅምር (startup) ከሞባይል አንቀሳቃሾችና ከገንዘብ ተቋማት ዳታ የሚያገኝ ሲሆን ይህን ዳታ የደንበኞችን የገንዘብ አቋም እና የመክፈል አቅም ዝርዝር ሁኔታ ለማስቀመጥ ይጠቀምበታል። ከሞባይል ገንዘብ አገልግሎቶች የሚሰበሰብ ዳታ የሰዎችን የገንዘብ አወጣጥ እና የቁጠባ ልማድም ለማወቅ ጠቀሜታ አለው። የሰዎችን የመክፈል ባህል በማየት ለወደፊቱ ምን ያህል የመክፈል አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል። የግዙፍ ዳታ መተንተኛ ቴክኖሎጂዎች ግሎባል ፐልስ በግዙፍ ዳታ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶችን በመጥቀስ እንደጻፈው አለም ላይ 2005 የነበረው የዲጂታል ዳታ መጠን 150 ኤክሳባይት(exabytes) ሲሆን ይህ አሃዝ 2010 ወደ 1200 ኤክሳባይትስ አድጓል። በሚቀጥሉት አመታትም የዲጂታል ዳታ በየአመቱ 40 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ 2007 እስከ 2020 ባሉት አመታት ዲጂታል ዳታ 44 እጥፍ እንደሚደርስ ያመላክታል። ስለዚህ ይህን በየጊዜው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለውን የዳታ መጠን እና አይነት መያዝ እና መተንተን የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ያስፈልጋል። እንደነ ኦራክል ያሉ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ግዙፍ ዳታን ለማከማቸት እና ለመተንተን የሚያስችሉ  የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ ላይ ናቸው። ኦራክል የተለያየ አይነት ያላቸው የግዙፍ ዳታ መተንተኛ ሶፍትዌሮችን በማቅረብ ላይ ይገኛል። ከነዚህ መተንተኛዎች ውስጥ ኦራክል ቢግ ዳታ ስፓሻል እና ግራፍ፣ ኦራክል አር ኢንተርፕራይዝ፣ ኦራክል ቢግ ዳታ ኤስ ኪዩ ኤል፣ ኦራክል ቢግ ዳታ ዲስካቨሪወዘተ መጥቀስ ይቻላል። 

  • ሃዱፕም(Hadoop)

ሌላው የግዙፍ ዳታ መተንተኛ እና ማከማቻ ሶፍትዌር ነው። ከነዚህ በተጨማሪ ገበያ ላይ በርካታ የግዙፍ ዳታ ማከማቻ እና መተንተኛ ሶፍትዌሮችና ሃርድዌሮች ይገኛሉ።

የግዙፍ ዳታ ፈተናዎች ትልልቅ ኮርፖሬሽኖች ግዙፍ ዳታን ተደራሽ የማድረግ ፍላጎታቸው አነስተኛ ነው። ኮርፖሬሽኖቹ ዳታን የማጋራት ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳ ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ስምምነቶች እንዲደረጉ ይፈልጋሉ። ስምምነት ከተደረሰም በኋላ ተመራማሪዎች በተለያዩ ሲስተሞች መካከል ያለው ያለመጣጣም ፈተና ይገጥማቸዋል። ከግዙፍ ዳታ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላው ፈተና ግለመብትና የዳታ ጥበቃ ነው። ከእያንዳንዱ ግለሰብ የሚሰበሰብ ዳታ የአንድን ሰው ግላዊነት የመቀነስ አቅም አለው። ግዙፍ ዳታ ለደህንነት ጥሰትም የተጋለጠ ነው። የዳታ ደህንነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ የሸማቾች እምነት ስለሚሸረሸር ከግዙፍ ዳታ የሚገኝ ጥቅም ያነሰ ይሆናል። የዳታ ምንጭ ማወቅም አንዱ የግዙፍ ዳታ ፈተና ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በስሙ የተመዘገበ ሲም ካርድ ለሌላ ሰው ቢሰጠው የቴሌኮም አንቀሳቃሽ የሚሰበስበው ዳታ በተመዝጋቢው ስም በመሆኑ የዳታ ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። ከዳታ ውክልና ጋር ተያይዞ የሚነሳ ፈተናም አለ። የግዙፍ ዳታ ምንጮች በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ የሚሰበሰበው ዳታ ቴክኖሎጂውን ከሚጠቀሙ አካላት ብቻ ነው። ስለዚህ ግዙፍ ዳታን መሰረት በማድረግ ስለአጠቃላይ ሁኔታ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ይሆናል። ግዙፍ ዳታ ከፍተኛ ክህሎትና ቅንጅት የሚጠይቅ ነው። ዘርፉ የበርካታ የሙያ ዘርፎችን ቅንጅት እና እውቀት የሚጠይቅ መሆኑ እነዚህን የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማቀናጀት ፈታኝ ነው።

የግዙፍ ዳታ ስታንዳርዳይዜሽን ሸማቾች እና ተቋማት ከግዙፍ ዳታ የሚያገኙትን ጠቀሜታ ለማሳደግ የበርካታ ነባርና አዳዲስ ሲስተሞችና ቴክኖሎጂዎች ቅንጅት ያስፈልጋል። የቴክኖሎጂ ቅንጅት እንዲኖር በግዙፍ ዳታ የእሴት ሰንሰለት መሃል ያለውን መጣጣም የሚያቀላጥፍ ደረጃ ያስፈልጋል። ሸማቾች የግዙፍ ዳታ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ቁሶችን ወይም

መተግበሪያዎችን ሲገዙ ከአንድ አቅራቢ ወይም አምራች ጋር ብቻ እንዳይታሰሩ የሚገዙዋቸው ምርቶች ሌሎች ከሚያቀርቡዋቸው ምርቶች ጋር መጣጣማቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የደረጃዎች መዳቢ ማህበረሰብ ግዙፍ ዳታን አስመልክቶ የተለያዩ ጅማሮዎችንና የስራ ቡድኖችን አቋቁሟል። ለምሳሌ የክላውድ ሴክዩሪቲ ጥምረት የግዙፍ ዳታ የስራ ቡድን 2012 ያቋቋመ ሲሆን ከዳታ ደህንነት እና የግለመብት ችግሮች ጋር የተያያዙ ቴክኒኮች በመለየት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ለማመቻቸት ያለመ ነው። የዚህ ቡድን ውጤት ከግዙፍ ዳታ ጋር የተያያዙ የደህንነት እና የግለመብት ተግባራት ግልጽ በማድረግ መንግስታትንና ኢንዱስትሪውን የሚመሩ ምርጥ ተሞክሮዎች ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። አለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረትም ከግዙፍ ዳታ ጋር በተያያዘ ቴክኒካዊ ደረጃ እና ፖሊሲ ለማውጣት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። የአሜሪካው ብሄራዊ የሳይንስና ደረጃዎች ተቋም የግዙፍ ዳታ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን አለም አቀፉ የደረጃዎች ድርጀትም በግዙፍ ዳታ እና የመጪው ትውልድ ትንተና ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ነው። ከነዚህ ተቋማት በተጨማሪ የወርልድ ዋይድ ዌብ ኮንሰርቲየምም ከግዙፍ ዳታ ጋር የተያያዙ በርካታ ማህበረሰቦችን ፈጥሯል። በአጠቃላይ ሲታይ የግዙፍ ዳታ የደረጃ ምደባ እና አወጣጥ ገና በጅምር ላይ ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ግዙፍ ዳታ ኢትዮጵያ ላይ ያለው አንድምታ በኢትዮጵያም የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ነው። ለምሳሌ እስከ ሰኔ 2007 . የነበረው የተንቀሳቃሽ ስልክ ተመዝጋቢ 40 ሚልየን የደረሰ ሲሆን  ተጠቃሚዎች የሚፈጥሩት ዳታ እየገዘፈ የሚሄድ መሆኑን መገመት ይቻላል። ስለዚህ በኢትዮጵያ እየሰፋ እና እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለውን ዳታ ለልማት እንዴት ማዋል ይቻላል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእያንዳንዱ የጊዜ መለኪያ የሚገኝ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ዳታ የሀገርን ልማት ከመደገፍ አንጻር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው። ነገር ግን ግዙፍ ዳታ ከሚፈጥራቸው መልካም አጋጣሚዎች ተጠቃሚ ለመሆን ዳታን በተገቢው መንገድ የመሰብሰብ፣ የማቀናበር እና የመተንተን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው።