Asset Publisher

null በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በአ.ብ.ክ.መ የከተማ ልማት ክላስተር መካከል የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)፣ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት (አ.ብ.ክ.መ) የከተማ ልማት ክላስተር ቢሮ መካከል የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ፡፡ ስምምነቱ በዋናነት የአ.ብ.ክ.መ ከተሞችን ወደ ስማርት ከተሞች ለማሻገር የሚደረግ የመሰረተ ልማት ግንባታን የመገንባት፣ እንዲሁም የካዳስተርና የመሬት አስተዳደር ቴክኖሎጂ የማበልጸግና መሰረተ ልማቶች ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

በስምምነቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአ.ብ.ክ.መ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አህመዲን መሃመድ ባስተላለፉት መልእክት ስምምነቱ የክልሉን የቆዩና እና አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል፣ በተለይም ህገ-ወጥ የመሬት ወረራንና ወንጀልን ለመከላከል፤ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና ከመጫወቱም በላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት ኢመደአ ቁልፍ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነትን በማረጋገጥ ለአገሪቱ የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ መርሃ ግብሮች ማስፈፀሚያ እንዲሆኑ በማስቻል የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም እንደሆነ አስታውሰው የሳይበር ቴክኖሎጂዎች ለአገራዊ ሁለንተናዊ እድገት መሰረት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደገለጹት ኢመደአ ያበለጸጋቸዉ የሳይበር ቴክኖሎጂ ምርቶች አሁን ላይ በተለያየ መልኩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና “ለዲጂታል 2025 ኢትዮጵያ” መደላድል በመፍጠር ሰፊ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ በዛሬዉ እለት ከአ.ብ.ክ.መ የከተማ ልማት ክላስተር ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም ኢመደአ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያለማቸዉን የቴክኖሎጂ ምርቶች ክልሉን በማስታጠቅ፣ የሰዉ ኃይሉን በማሰልጠን እንዲሁም የክልሉን ሴክተር መስሪያ ቤቶች በማዘመንና ከጥቃት በመከላከል ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የበኩሉን ሚና ለመጫወት እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ቴክኖሎጂ የአገልግሎት ዘርፉን በማቀላጠፍና ምርታማነትን በማሻሻል ረገድ ያለው ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑን አመላክተው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለሙትንና ተግባራዊነታቸው የተረጋገጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አ.ብ.ክ.መ. በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ ተቋማቸው ሙሉ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለሙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አገልግሎቶች ምን እንደሚመስሉ እንዲሁም የአ.ብ.ክ.መ ከተማ ልማት ክላስተርን አሰራርና አገልግሎት በማዘመንና በማቀላጠፍ ረገድ ከየትኛው ዘርፍ ጋር የበለጠ እንደሚቀናጁ ዝርዝር ማብራሪ ቀርቧል፡፡ በዚህም በክልሉ ያሉ ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር የካዳስተር ስርዓትን የተከተሉ፣ ወሳኝ መሰረተ ልማት የተሟላላቸዉ፣ መልካም አስተዳደር ስራን የሚደግፉ፣ ከተሞች የልማትና የአገልግሎት ማዕከል እንዲሆኑ፣ የሴፍሲቲ ዲዛይን እና ግንባታ እንዲሁም የስማርት ሲቲ ሮድማፕ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የሚየስችሉ የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶችን ለክልሉ በማስታጠቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡