Asset Publisher

null የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል የትብብር መግባቢያ ስምምነት በአራት የመንግሥት ተቋማት መካከል ተደረገ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል “የካፒታል ገበያ የመንግስት ተቋማት የቴክኖሎጂ ግብረ ሃይል” በሚል ማዕቀፍ የትብብር መግባቢያ ስምምነት በአራት የመንግሥት ተቋማት መካከል ተደረገ፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት እና በጠቅላይ ሚስቴር ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ናቸው፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መቋቋም የሐገሪቱን የኢኮኖሚ ሴክተር በመሰረታዊነት ለመለወጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን በሐገር ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚናን የሚጫወት ተቋም ለመደገፍ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘው እንደገለጹት የካፒታል ገበያ ተዋናዮች የሚጠቀሟቸው ማናቸውም የኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓቶች በትክክል መሥራት አለመስራታቸውን መፈተሽ እና የግንኙነት አውታሮቹ ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይፈጸም በተቀናጀ ሁኔታ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ መከላከል የኢመደአ ዋና ድርሻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር የመረጃ ደህንነት እና የዳታ ጥበቃ ድጋፍ በማድረግ ሐገራዊ የዳታና ዲጂታል ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ረገድ ኢመደአ የራሱን ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ወ/ሮ ትዕግስት ለዚህም ለካፒታል ገበያ ሥርአት የሚያስፈልጉ ሲስተሞችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በራስ አቅም በማልማት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን የማስታጠቅ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የዲጂታል ፎረንሲክ አገልግሎት፣ የሴኪዩሪቲ ክሊራንስ፣ የሳይበር ጥቃት ክትትልና መከላከል መስጫ ማዕከል እንዲደራጅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ሌሎች ለባለስልጣኑ የሚደረጉ ድጋፎች መሆናቸውን ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ታዬ በበኩላቸዉ የመግባቢያ ስምምነቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ እየተቋቋመ ከሚገኘው የካፒታል ገበያ ጋር በተገናኘ በተቋማቱ መካከል ቋሚና ዘላቂ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት በመፍጠር የካፒታል ገበያን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የካፒታል ገበያ ተገበያዮችን ባህሪ በማጥናት እና ለአደጋ የሚዳርጉ ተግባራትን አስቀድሞ በመለየት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን የመደገፍ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የካፒታል ገበያን የግብይት ሥራዓት በጋራ በማበልጸግ የፋይናንስ የቴክኖሎጅ እና የእውቀት ሽግግር ድጋፍ እንደሚደረግም ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚስቴር ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በካፒታል ገበያ ሥርአት ውስጥ ወሳኙ ጉዳይ “ደንበኛን ማወቅ - Know You Customer” መሆኑን ጠቁመው ይህንን እውን ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የራሱን ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያ ተገበያዮችን ማንነት በመለየት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ማንነት ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ ድጋፍ በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ አቶ ዮዳሄ ገልጸዋል፡፡