የሐገራችንን የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የዓድዋን ድል በዘመናችን የመድገም ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን - ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፡የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር
የሐገራችንን የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት በማረጋገጥ የዓድዋን ድል በዘመናችን የመድገም ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን - ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፡የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር
128ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በንግግራቸው የዓድዋ ድል ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና ለአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት መሆን የቻልንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው ብለዋል። ይህንን አኩሪ ገድል በዘመናችን የጦርነት አውድ በሆነው የሳይበር ምህዳር ላይ በመድገም የሐገራችንን የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ በታሪክ አጋጣሚ የተረከብነው አደራ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የድል በአል ስናከብር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ግን የነጻነት ቀናቸውን ያከብራሉ፡፡ ይህ የሆነው ጀግኖች አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሉዓላዊት ሀገር ስላስረከቡን አንደሆነ ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን አንድም ቀን በሀገራዊ ክብር እና ሉአላዊነት ላይ ተደራድረው እንደማያውቁና በትናንሽ ቁርሾዎችና ልዩነቶች ምክንያት የአገር ህልውና፣ ነፃነት፣ ክብር አሳልፈው እንዳልሰጡ አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘው እንደገለጹት ይህ ወቅት ከአድዋ ጀግኖች ብዙ የምንማርበት ብሎም የዛሬው ትውልድ ችግሮቹን በዓድዋ መንፈስ እንዲፈታ የቤት ሥራ የምንቀበልበት ነው ብለዋል።
ዛሬ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር የሚረጋገጠው ዜጎች በሳይበር ምህዳር ላይ የጎላ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱና ምህዳሩ በሀገር በቀል እውቀት፣ ፍልስፍና፣ አስተሳሰብ፣ ባህል እና እሴት መገራት ሲጀምር ብቻ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህ መሆን ካልቻለ በዘርፉ የላቁ ሀገራት በራሳቸው አስተሳሰብና ፍላጎት ባህልና ወግ ተንተርሰዉ ላለሙትና መስፈርት ላወጡለት ቴክኖሎጂ ጥገኛ መሆናችን አይቀሬ ነው። ይህ ጥገኝነት ደግሞ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ ደማቸዉን አፍስሰዉ በክብር የሰጡንን የአድዋ ጀግኖችን አደራ መዘንጋት ነው ብለዋል።
በሳይበር ምህዳሩ የምንሰራቸዉ ስራዎች በአድዋዉ የድል ወኔ፣ የአንድነትና የመደመር መንፈስ መስራት ካልተቻለ እጅግ አስቸጋር ምህዳር ዉስጥ እንደመሆናቸን መጠን የሃገራችንን የሳይበር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እና ሀገራዊ ክብር ማረጋገጥ የማይታሰብ ይሆናል።በመሆኑም ሐገራችንን ወደ ብልጽግና ማማ ማድረስና ልክ እንደ አደዋው ዘመን ሁሉ በጠላቶቿም ሆነ በወዳጆቿ በክብር የምትታይ የአፍሪካ ዕንቁ ማድረግ ዋና ግባችን ቢሆንም ይህ የሚሳካዉ በተሰማራንበት አዉድ የዘመን አደራና የትዉልድ ግዴታችን መወጣት ስንችል ነዉ ሲሉ ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸው፤ ከአድዋ የተረከብነውን የአሸናፊነት፣ የፅናትና የጀግንነት መንፈስ የሳይበር ደህንነትን በማስጠበቅ እና የዲጂታል ሉአላዊነትን በማስከበር ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ተቋም የተሰጠንን ሃላፊነት በላቀ ቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል እንገባለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ስለ አድዋ ድል ሰፊ ታሪካዊ ትንታኔ ያቀረቡ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ባቀረቡት ንግግር የአድዋ ድል ቁልፍ ሚስጥር አንድነትና ጀግንነት መሆኑን አስረግጠዋል፡፡ የቀጣዩ ዘመን ጦርነት ግን ከአካላዊ ውጊያ ይልቅ ወደ ዲጂታሉ ቴክኖሎጂ የሚያመዝን በመሆኑ የዘመኑ ትውልድ አንድነቱን አስጠብቆ የቴክኖሎጂና የእውቀት ባለቤት በመሆን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ መዘጋጀት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አያይዘው እንደተናገሩት ሐገራችን ከምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና እና አጠቃላይ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና የተፈጥሮ ጸጋዎች ጋር ተያይዞ በውጭ ሃይሎች ዘንድ ለጥቃት ተጋላጭ መሆናችንን ጠቅሰው፤ ይህንን ለመከላከል በአንድ በኩል በሁለንተናዊ መስኩ ብቁና ጠናካራ የመከላከያ ሃይል መገንባት፤ በሌላም በኩል ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ቀዳሚ መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡