የሳይበር ቻሌንጅ ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ምዝገባ ግንቦት 24 ይጠናቀቃል
የሳይበር ቻሌንጅ ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ምዝገባ ግንቦት 24 ይጠናቀቃል
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የሚያዘጋጀው 4ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሳይበር ቻሌንጅ ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ምዝገባ እሁድ ግንቦት 24 /2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ::
በኢመደአ የሳይበር ልሕቀት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ቢሻው በየነ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ2017 ዓ.ም ለ4ኛ ዙር ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸዉን ታዳጊዎች በመመልመል ሀገራችን ሊገጥማት የሚችለውን ውስብስብ የሳይበር ጥቃት መከላከል የሚያስችል ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችን ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት ለማሳካት እንዲሁም የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ የሳይበር ታለንት ልማት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የገለፁት አቶ ቢሻው፤ ይህንን በመገንዘብም በኢመደአ የሳይበር ልህቀት ማዕከል ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ሰመር ፕሮግራም በማዘጋጀት በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ባለ ተሰጥዖዎችን በዘርፉ ሲያለማና ሲያበቃ መቆየቱን ገልጸዋል::
ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የተከናወነውን መነሻ በማድረግም በ2017 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ ፕሮግራም ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን በሳይበር ደህንነት፤ በዴቨሎፕመንት፤ በኢምቤድድ ሲስተም እና በኤሮስፔስ ላይ ልዩ ተሰጥኦ እና ፍላጎት (Talent with passion) ያላቸው እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል::
በመጨረሻም የዘንድሮው የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ ፕሮግራም ከሌላው ጊዜ የሚለየው የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ተመዝጋቢዎች የበለጠ እድል እንደሚያገኙ ተገልጿል::