በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረዉ ክስተት ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ እንጂ ከውጭ አካላት የተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረዉ ክስተት ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ እንጂ ከውጭ አካላት የተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ትኩረቱን የፋይናንስ ተቋማት፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን የሚያስተዳደሩ ተቋማት፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት ላይ በማድረግ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ አንጻርም በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ስርዓት ላይ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የደህንነት ፍተሻ ማድረጉን ወ/ሮ ትዕግስት ገለጸዋል።

በተደረገው የሳይበር ደህንነት ፍተሻ መሰረትም የተፈጠረዉ የሲስተም ችግር ከውጭ አካላት በተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት ምክንያት መሆኑን የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘም። ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በምርመራ የተለዩ ሲሆን ይህም ባንኩ በሞባይል ሲስተሙ ላይ ባደረገዉ ማሻሻያ መሆኑን ለማወቅ እንደተቻለ ወ/ሮ ትዕግስት ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘው እንደገለጹት በባንኩ በቅርቡ ተሻሽሎ በቀረበው “Source Code” ላይ የፕሮግራሚንግ ቅደም ተከተል ወይም ሎጂካል ፍሰት የተዛባ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል። በዚህም ገንዘብ የሚያወጡ የባንኩ ደንበኞች ገንዘብ ሲያወጡ ሲስተሙ መቀነስ የነበርበትን መጠን ሳይቀንስ እና ባላንስ ለመስራት ወይም ለማመዛዝን አመቺ ሁኔታ ሳይፈጥር ክፍያ ይፈፅም እንደነበር የምርመራ ዉጤቱ ያሳያል። በምርመራ ሂደቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውስጥም ይሁን ከውጭ ለሚቃጡበት የሳይበር ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለዉና አስፈላጊውን የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በባንክ ሲስተሞቹ ላይ የተደረገዉ ፍተሻ እንደሚያሳይ ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል።

የጥቃቱን አይነት ለመለየት በተደረገ ጥልቅ ትንታኔ መሰረት ከውጭ ወደ ባንኩ ሰርጎ በመግባት የደረሰ ምንም አይነት አደጋ አለመኖሩን ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ተጨማሪ ምርመራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ወ/ሮ ትዕግስት ተናግረዋል።

የባንኩ ደንበኞችም ሆነ የትኛዉም ማህበረሰብ በባንኩ ላይ የተፈጠረዉ ክስተት ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮች መሆናቸዉን በመረዳት በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ባንኩ ዘርፈ ብዙ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት እየተናፈሰ ያለው ወሬ መረጃ ላይ መሰረት ያላደረገ መሆኑ ተገንዝቦ በማኛውም ወቅት ትክክለኛ የሆኑ የመረጃ ምንጮችን ብቻ እንዲከታተል ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገራችንን የሳይበር ስነ ምህዳር ደህንነት ለማረጋገጥ 24/7 ስራዎች እየሰራ የሚገኝና ከዉስጥም ሆነ ከዉጭ አካላት የሚሰነዘሩ ማንኛዉንም ዓይነት የሳይበር ጥቃት እያከሽፈ የመጣ፤ ተቋማት የሳይበር ጥቃቶች እንዳይደርስባቸዉ የሚጠቀሙባቸዉን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ኦዲት በማድረግና ክፍተቶችም ካሉ እንዲደፍኑ ምክረ-ሃሳቦችን በመስጠት በኢትዮጵያ የሳይበር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን የማክሸፍ ሃላፊነቱን እንደወትሮው ሁሉ በብቃት እንደሚሰራ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል።