ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ከሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗ ተገለጸ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ከሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት በሩዋንዳ ኪጋሊ፣ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የሳይበር መከላከያ ፎረም 2023 ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።

ኢትዮጵያን ወክለው በስብሰባው የተገኙትና መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ሰለሞን ዓለም በፍጥነት ወደ ሳይበር ቴክኖሎጂ እየተሸጋገረች በመሆኑ ለአንድ ሀገር ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የሀገሪቱን የመረጃ እና የመረጃ መሠረተ ልማቶችን ደህንነት ብሎም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን (ኢመደአ) በአዋጅ አቋቁማ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ አመታት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን በፎረሙ ላይ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የቴክኖሎጂ ባለቤት ከመሆንና ፈጠራን ከማበረታት ጋር ተያይዞ በዘርፉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች በመመልመል፣ በማልማት ተሰጧቸዉን አሟጠው ሊጠቀሙበት እና የበለጠ ሊያጎለብቱበት የሚችሉበትን አዉድ ማለትም የታለንት ልማት ማዕከል በማቋቋም ዉጤት መምጣት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በመለስ ኢመደአ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቋማትን በመገንባት እና የሳይበር ምህዳሩን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማስቻል አኳያ ሰፊ ሰራዎችን እየሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን፣ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጆች እና ሌሎችም የቁጥጥር ማዕቀፎች በማርቀቅ እና በማጸደቅ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል አቅሟ ከፍ እያለ መምጣቱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ እንደ ተቋም ኢመደአ ከመንግስትና ከግል ተቋማት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት መቻሉ የመከላከል አቅም ማደግ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 የበጀት ዓመት በሀገሪቱ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል በመቻሏ 23.2 ቢሊዮን ብር ማዳኗን በመድረኩ አንስተዋል።

ኢመደአ በኢትዮጵያ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ከመከላከል ባለፈ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አንዱ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት እንደ መርህ መዉሰዷን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን በራስ አቅም ቴክኖሎጂን ማበልጸግና መጠቀም የዲጂታል ቅኝ ግዛትን ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ ነዉ ብለዋል።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የዲጂታል ቅኝ ግዛትን ለመከላከል እያደረገች ያለዉን ጥረትና ዉጤት ለሌሎች ወንድም አፍሪካ ሀገራት ተሞክሮዋን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፣

የአፍሪካ ሀገራትም እርስ በርሳቸዉ ከሚፈጥሩት ትብብርና አጋርነት በመለስ በራሳቸዉ አቅም የበለጸጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ወደ ሳይበር ምህዳሩ በማምጣት የዲጂታል ቅኝ ግዛትን መከላከል እንደሚገባ በፎረሙ አመላክተዋል።

እንደ አፍሪካ በሳይበር ዲፕሎማሲ ዘርፍ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋትና ግንኙነትን በማጠናከር በሳይበር ስነ ምህዳሩ የሚፈጠሩ መልካም እድሎችን በጋራ መጠቀምና አደጋዎችንም በጋራ መከላከል ይገባናል ብለዋል።

እንደ ሀገር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ከየትኛዉም ፍቃደኛ ከሆነ ሀገር ጋር ለመስራት ተነሳሽነት እና ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።

Asset Publisher


የቅርብ ዜናዎች