የአፍሪካ ሕብረት የሳይበር-ደኅንነት እና ግላዊ መረጃ ጥበቃ ኮንቬንሽን መፈረምና መቀበልን በተመለከተ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ውይይት ተካሄደ
የአፍሪካ ሕብረት የሳይበር-ደኅንነት እና ግላዊ መረጃ ጥበቃ ኮንቬንሽን መፈረምና መቀበልን በተመለከተ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ውይይት ተካሄደ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የአፍሪካ ሕብረት የሳይበር-ደኅንነት እና ግላዊ መረጃ ጥበቃ ኮንቬንሽን (ማሌቦ ኮንቬንሽን) መፈረምና መቀበልን በተመለከተ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኮንቬንሽኑ ድንበር-ተሻጋሪ የሳይበር-ወንጀሎችን ለመመከት፤ ያሉብንን የሳይበር-ደኅንነት የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችን ለመሙላት፤ ከአቻ የአፍሪካ ሃገራት ጋር በዘርፉ በጋራ ለመስራት፤ የኢንቨስትመንት በር ለመክፈት፤ ፖለቲካዊና ቴክኖሎጂያዊ ጠቀሜታዎች ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኮንቬንሽኑ በዋናነት በሦስት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ይኸውም የኤሌክትሮኒክ ግብይትን፣ የሳይበር-ደኅንነትን ማሳደግና የሳይበር-ወንጀልን መዋጋትን እንዲሁም ግላዊ መረጃ ጥበቃን የያዘ ነው፡፡
በውይይቱም ኢትዮጵያ ይህን ኮንቬንሽን ተቀብላ ብታጸድቅ የሚኖረው ፋይዳ፣ ገደብ እና አስገዳጅነት እንዲሁም መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ጥያቄዎችና አስተያቶች የተሰነዘሩ ሲሆን ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት፣ አስተያቶቹን ደግሞ እንደግብአት በመውሰድ ጥናቱን ለማዳበር እንደሚውሉ በመድረኩ ተገጿል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የሳይበር ደህንነት እና ግላዊ መረጃ ጥበቃ ኮንቬንሽን በኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማሌቦ እ.አ.አ በ2014 የወጣ ሲሆን ከ9 ዓመታት በኃላ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስፈልጉት የፈራሚ ሃገራት ቁጥር (15) በማሟላት በሰኔ 2023 ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ኮንቬንሽን ፈርማ ለመቀበል እንድትችል ከሁለት ዓመታት ለበለጡ ጊዜያት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥናት ሲደረግ የቆየ ሲሆን የሳይበር ምህዳር ድንበር ተሸጋሪ እንደመሆኑ መጠን ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ቀጠናዊ ትብብርና ትስስር መፍጠር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡