ማሕበራዊ ሚዲያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ
ማሕበራዊ ሚዲያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና ሜታ ኩባንያ በጋራ በመሆን ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ ሚኒስቴር መ/ቤቶች እና መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ የዲጂታል ሚዲያ አስተዳዳሪዎች እና ባለሙያዎች ተቋማዊ የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾችን ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጡ።
ስልጠናው በዋናነት የተቋማትን የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾች የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎች በተጨባጭ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች መፍታት የሚችሉባቸውን እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ያስቻለ ነበር፡፡
ማሕበራዊ ሚዲያን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በውጤታማነት ለመጠቀም የሚዲያዎቹን ባሕሪና ማኅበረሰባዊ የአጠቃቀም ፖሊሲ መጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ በስልጠናው ወቅት ተገለጿል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው ወቅት በተጨባጭ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተው ውይይት አድርገውባቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መካከልም፤ የገጽ መጠለፍ፣ አላስፈላጊ ይዘት በአካውንታቸው ላይ መለጠፍ፣ የተቋማቸውን የማሕበራዊ ሚዲያ ገጽ ስም ለመቀየር መቸገር፣ ሀሰተኛ ተመሳሳይ ገጾችን ለማስወገድ መቸገር፣ አካውንታቸው ቢዘጋ ወይም ቢታገድ በምን መልኩ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው አለማወቅ ወ.ዘ.ተ በዋናነት የተነሱ ተግዳሮቶች ሲሆኑ፤ እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ የኢመደአ እና የሜታ በለሙያዎች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡