በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሀገራችንን የቴክኖሎጂ እድገት ያሳዩ ናቸው

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሀገራችን የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ባለቤትነትን በማረጋገጥ ከፍ ያለ ደረጃ መድረሷን ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

ይህ የተባለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ወሳኝ የሆኑ የሀገሪቱን የደህንነት፣ የመሰረተ ልማትና የፋይናንስ ተቋማት ከሳይበር ጥቃት በመከላከል ረገድ እያከናወነ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ቋሚ ኮሚቴውም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሶስት ፈረቃ ለ24 ሰዓታት የሚሰራ የሳይበር ሰራዊት ማሰማራቱን፤ በሳይበር ደህንነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ከመስራትም ባለፈ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሳይበር ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ተቋሙ ያለማቸውን ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶች የመጠቀም ባህል አለመዳበሩ እንዲሁም የተሻለ ደሞዝና ጥቅማጥቅም ፍለጋ ወደ ሌላ ተቋም የሚፈልሱ ባለሙያዎች ለቀጣይ ስራ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ተቋሙ እያከናወነ ያለው ተግባር በኢትዮጵያ እድገት ላይ ትልቅ ተስፋ እንዲኖራቸው ማድረጉን ገልጸው፤ ተቋሙ ያለማቸው ሶፍትዌሮች ለውጭ ጥቃት የማይጋለጡ በመሆናቸው የመንግስት ተቋማትም ሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ እንዲጠቀም መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የማህበራዊ ሚዲያን ለአሉታዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖችን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚያስፈልግ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡