ኢመደአ ከኢጋድ የሴኪዩሪቲ ሴክተር ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለአባል ሃገራቱ ተወካዮች በድሮን ቴክኖሎጂ ልማትና ደህንነት ዙሪያ ስልጠና ሰጠ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት (IGAD) የሴኪዩሪቲ ሴክተር ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለአባል ሃገራቱ ተወካዮች በሰው አልባ በራሪ ቁሶች (Drone)  እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሳቢያ የሚደርሱ ቀጠናዊ የጸጥታ ችግሮችን በመከላከል ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡

ለአምስት ቀናት በቆየው ተግባራዊ ስልጠና (Workshop) ላይ ከስምንት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ተወካዮች ተካፍለዋል፡፡በስልጠናውም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚደርሱ የጸጥታ ችግሮችን በተለይም ደግሞ በሰው አልባ በራሪ ቁሶች (Drone) እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች (Emerging Technologies) ሳቢያ የሚደርሱ የጸጥታ ችግሮችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክርና ስልጠና ተካሂዷል፡፡

በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አባላት እንደተናገሩት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግና ለዚህም በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላም የአባል ሃገራቱ ተወካዮች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይ የድሮን ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሌሎች የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማቶች ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኢመደአ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ለአባል ሃገራቱ ተወካዮች የኢመደአን የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት አቅም ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ይህንን የተቋሙን አቅም ወደሌሎች የቀጠናው ሃገራት በማስፋት በጋራ ማደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘው እንደገለጹት ኢመደአ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ለቀጠናው አባል ሃገራትም አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ለመላቀቅ በራስ አቅም ላይ የተመሰረተ የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ማካሄድ ያስፈልጋል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ረገድ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በአጠቃላይም አፍሪካውያን ያላቸውን እምቅ አቅም አስተባብሮ በመስራት በቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡

የአባል ሃገራቱ ተወካዮች በኢመደአ በነበራቸው ጉብኝት የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂና የሳይበር ደህንነት አቅም ማየት እንደቻሉ ገልጸው ኢመደአ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እየሄደበት ያለው ርቀት ለቀጠናው ሃገራት ምሳሌ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡