127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አአስተዳደር (ኢመደአ)፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አመራሮች እና አባላት 127ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በደማቅ ሁኔታ አከበሩ፡፡
በበአሉ ላይ የተገኙት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካይ አቶ ጥላሁን ጣሰው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት አባት እና እናት አርበኞች ከምእራባውያን ወረራ በጽናት ታግለው አገራችንን እንዳቆዩ ሁሉ የአሁኑም ትውልድ ከማንኛውም ጥቃት እና ተጽእኖ ሀገሩን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው የዓድዋ ድል በዓል በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኩራት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጥቁር ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው የሄዱበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ግን ታሪክ እንደሆነ እና ለአሁኑ የሀገር እድገት እና ሉዓላዊነት መሰረት እንጂ ዋስትና እንደማይሆን አስረድተው፤ ትውልዱ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ባለቤት በመሆን ከምእራባውያን ጥገኝነት ነጻ በመውጣት ደማቅ ታሪክ ሰርቶ ድሉን ማስቀጠል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደገለጹት ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት እውቀትን በመታጠቅ ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን ድል ማድረግ ነው ብለዋል፤ ይህ ግን እንዲሁ በነጻ የሚገኝ ሳይሆን መስዋእትነትን በመክፈል ጭምር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የአድዋ ድል ጀግኖች ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ነጻ ሃገር እንዳስረከቡን ሁሉ የዛሬው ትውልድም ድህነትን በእውቀትና በጥበብ ጦር ድል በማድረግ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ኢመደአ የሃገራችንን የሳይበር ደህንነት በመጠበቅ የዲጂታል ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ልክ እንደ አድዋ አርበኞች ሁሉ በጀግንነት እና በጽናት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚንስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው ዛሬም ወረራ መልኩን ቀይሮ በቴክኖሎጂ እና በባህል እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ገንዘብ ከፍለን በምንጠቀምበት ማህበራዊ ሚዲያ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያፈርስ ተልእኮ እየገዛን እርስ በእርሳችን በመገዳደል የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ከሚጥል ተግባር መቆጠብ እና የአባቶቻችንን አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት ወስደን የተሻለ አገር መገንባት እንደሚገባን አሳስበዋል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ባስተላለፉት መልዕክት የአድዋ ድል ጀግኖች አንድነትን ሃይል በማድረግ በጀግንነት እና በጽናት ታግለው ጠላትን ድል እንዳደረጉ ሁሉ የዛሬው ትውልድም አንድነቱን፣ ጀግንነቱን እና ጽናቱን ድህነትን ድል ለማድረግ በሚደረገው ትግል ላይ በማዋል የበለጸግች ሃገርን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ግርማ በአሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ጥንት አባቶቻችን ጥቁር ሕዝብ በነጭ መገዛት አለበት የሚለውን አስተሳሰብ በጽኑ ተጋድሏቸው ቀይራዋል፡፡ እኛም ዛሬ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን እና ለመልካም ነገር በማዋል የሀገራችንን ሰላም እና ደህንነት አስጠብቀን ለሚቀጥለው ትውልድ ሌላ ድል ማስረከብ አለብን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል እና ተወካይ አቶ ጥላሁን ጣሰው የሀገርን አንድነት የመጠበቅ አደራን እና ሰንደቅ አላማውን ከአራቱም ተቋማት ለተወከሉ ወጣቶች አስረክበዋል፡፡