ባለፉት 9 ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተቻለ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

ባለፉት 9 ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተቻለ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2015 ዓ/ም:  የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በ2015 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ባከናወነው የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል ስራ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት የአስተዳደሩን የ2015 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው

 

ዋና ዳይሬክተሩ በዋናነት የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት፣ የሳይበር ደህንነት ስጋት፣ የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት እና የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥርን መሰረት አድርገው ዝረዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

2015 / በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በሀገራች 4422 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች የተፈፀሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 4272 ምላሽ የተሰጠባቸው እና 150 ያህሉ ጉዳት ያደረሱ መሆኑን አቶ ሰለሞን ሶካ ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰራቸው ስራዎች የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀሙን 94.86 ከመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል ፡፡

የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃ ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነት መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይደርስ ነበር ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸዉን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ማድረጋቸዉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፤ ሚዲያ ተቋማት፤ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የክልል ቢሮዎች የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

በሃገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ስለተከሰቱ ሳይበር ጥቃት አይነቶች እና ኢላማዎች ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፤ ማልዌር፤ የመሰረተ ልማት ቅኝት (Scan) የመሰረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS) ሰርጎመግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸዉ እንደነበሩ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም በተለያዩ ዘርፎች በሚገኙ 80 ተቋማት (34 የመንግስት እና 46 የግል) በተደረገ የተጋላጭነት ዳሰሳ ጥናት የዌብ፣ የኔትዎርክ መሰረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች  ላይ 486 የሳይበር ደህንነት የተጋላጭነት የአደጋ ደረጃ (Vulnerability risk level) ክፍተት መገኘቱን እና ከነዚህ ውስጥ 129 የሚሆኑት ከፍተኛ፣ 217 መካከለኛ እና 140 የሚሆኑት ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡       

በተጨማሪም አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 3123 የተለያዩ አይነት የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች መካከል  453 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው የተለዩ ቴክኖሎጂዎች በመሆናቸው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት አደጋ ደረጃ ለማመላከት በተመረጡ አራት ዘርፎች (የሚድያ ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የፀጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ቁልፍ መሰረት ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት) ላይ ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትን እና ተጋላጭነትን በማጣመር መሰራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በመመከት፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ሀገራዊ ጉዳቶች ማዳኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገራችንን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚሰራው ስራ አጠናክሮ በመቀጠል ብሔራዊ ጥቅማችንን በሳይበር ምህዳሩ ላይ ያስጠብቃል ሲሉ አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል፡፡