ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ማጎልበት ይገባቸዋል - የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ፡ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

4ኛዉ ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ሁለተኛ ሳምንት “አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሃገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጊዮን ሆቴል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል፡፡

4ኛውን የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ የተዘጋጀው ኤግዚቪሽን በክቡር ዶ/ር አብርሃም በላይ ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን “ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ስጋት” በሚል ርእስ የፓናል ውይይትም በጊዮን ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢንፍርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ባስተላላፉት መልእክት ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ማጎልበት፣ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶቻቸውን ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት መላቀቅና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነዉ ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ከሚፈታተኑ አበይት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ሲሆን በተለይም ሳይበር በባህሪው ድንበር የለሽ፣ ውስብስብ እና ኢ-ተገማች በመሆኑ አንድ ሀገር የሳይበር ደህንነት አቅሙን ካላሳደገ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱ እና ብሄራዊ ጥቅሙ ከፍተኛ አደጋላይ ይወድቃል ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት በሀገራችን የሳይበር ምህዳሩን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ጨምሮ በሀገራችን ቁልፍ የመንግስት መሰረተ-ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገራችንን ቁልፍ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነትን በማረጋገጥ ለሀገራችን የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ መርሃ ግብሮች ማስፈፀሚያ እንዲሆኑ የማድረግ እና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች የማስጠበቅ ስራዎችን እየሰራ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል።

በሳይበር ምህዳሩ ላይ የሚፈጠር የግንዛቤ እጥረት እና የአጠቃቀም ስህተት የችግሮች ሁሉ ምንጭ መሆኑን የተረዳዉ ተቋማችን ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና የሚፈጥሩ ሁነቶችን በማዘጋጀት እና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫና ባህል ግንባታ ሥራዎችን እየሰራን ቆይተናል ሲሉ አቶ ሰለሞን ሶካ ተናግረዋል።

4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መቀነስና ዝግጁነታቸውን ማሻሻል፤ ተቋማት ይህን ዓለማቀፍና ሃገራዊ ሁነት በራሳቸው አውድ ወስደው ተቋማዊ ንቅናቄን እንዲያደርጉ መደገፍ፤ በሀገራችን ሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ የግሉን ሴክተር ሚና ማሳደግ እና ማበረታታት ጨምሮ የሳይበር ደህንነት ጥናትና ምርምሮችን ማበረታታት ታሳቢ በማድረግ “አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሃገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪቃል እየተከበረ ይገኛል።

Asset Publisher


የቅርብ ዜናዎች