በ2015 የመጀመሪያ ሩብ አመት ብቻ ከ1600 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

በ2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት ብቻ ከ1600 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በኢትዮጵያ ላይ መሞከራቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ያሉት "የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለሃገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1/2015 እስከ ጥቅምት 30/2015 ዓ/ም ድረስ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የ4ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡

3ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የ4ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላቶች ተገኝተው በሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ወቅታዊና ቀጣይ አዝማሚያ ዙሪያ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት በ2015 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት በሃገራችን የተቃጡ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ዋነኛው ትኩረታቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው ላቅ ባሉ ማለትም ሆስፒታሎች፣ የትምህርት፣ የሃይል ማመንጫና ማሰራጫ ተቋማት፣ የፋይናንስ፣ የመከላከያና ደህንነት ተቋማት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች እና የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ስርአቶች ላይ ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ጥገኝነት እና ዝቅተኛ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የሳይበር ጥቃት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ከመከላከል አንጻር የሕብረተሰቡን ብሎም የተቋማትን የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ደረጃ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሃገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እና የአሰራር ስርአትን መዘርጋት በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በሃገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰውን ልጅ በማታለልና በማሳመን ሚስጥራዊ መረጃዎችን አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያደርገው ማህበራዊ ምህንድስና (Social Engineering) የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አቶ ሰለሞን ሶካ ገልጸዋል፡፡ ከማህበራዊ ምህንድስና በተጨማሪም "ዲፕ ፌክ" የተባለው ጥልቅ የሆነ የሳይበር ጥቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

ኢመደአ በሃገራችን ክልከላ ባለባቸውና አቅም ባልተፈጠረባቸው የሳይበር ቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ አቅም እየፈጠረ ቢሆንም ያለ ዜጎች የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ እድገት በቴክኖሎጂ ባለቤትነት ብቻ የሃገራችንን የሳይበር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ አይቻልም ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በ3ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ላይ ተሳታፊ የሆኑ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች የሃገራችንን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የእያንዳንዱ ዜጋ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በዘርፉ ላይ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ሰለሞን ሶካ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡