ሞሲፕ ኮኔክት (MOSIP Connect) የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ይገኛል

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በሕንድ ከሚገኘው Modular Open Source Platform (MOSIP) ከሚባለው የቴክኖሎጂ አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሞሲፕ ኮኔክት (MOSIP Connect) የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኮንፈረንሱ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት በአፍሪካ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው “MOSIP Connect 2024 ጉባኤ” የኢትዮጵያን የዲጂታል 2025 ርዕይ እውን ለማድረግ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጉልህ የሆነ የዲጂታል ለውጥ ጉዞ በማድረግ ላይ ትገኛለች ያሉ ሲሆን፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በሕዝብ ቁልፍ መሠረተ ልማት፣ በኢ- ንግድ፣ እና የሞባይል ክፍያ መፍትሄዎች ወ.ዘ.ተ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው ይህም በአገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለውጥ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሐገራችንን የሳይበር ደህንነትና ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ንጣፍ (core layers) የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የጉባኤው መዘጋጀት በዋናነት በዲጂታል የሕዝብ መሰረተ ልማት (Digital Public Infrastructure - DPI) ዙሪያ ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዲጂታል ፍኖተ ካርታ ስትራቴጂ ላይ የሚሳተፉ ዋና ዋና የመንግስት ተቋማት፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ከ500 በላይ ዓለም ዓቀፍ ተሳታፊዎች፣ ከ30 ሀገራት በላይ የተወጣጡ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሳተፉና አውደ ርዕይ የሚያቀርቡ ይሆናል። ኮንፍረንሱ ከየካቲት 26/2016 ዓ/ም ጀምሮ እስከ የካቲት 27/2016 ዓ/ም ድረስ በስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል፡፡