በቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ
በቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ
በቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በስካይላይት ሆቴል የምክክር መድረክ ተካሄዷል፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን አሹራንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሀኒባል ለማ እንዳሉት ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ፣ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እድገት የማይተካ ሚና አላቸዉ ።
በቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርስ የሳይበር ጥቃት በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እና በሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እና ጠንካራ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል ።
ሀገራዊ ፋይዳቸዉ ከፍተኛ የሆኑ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች የቴክኖሎጂ ትስስራቸው እያደገ በሄደ ቁጥር ለሳይበር ጥቃት የመጋለጥ እድላቸዉ ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ሀኒባል አሳስበዋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በዋናነት ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ለሃገር ግንባታ ካላቸው ፋይዳ አንፃር የወጣባቸው ኢንቨስትመንትም ከፍተኛ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ነው አቶ ሀኒባል የተናገሩት።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ቁልፍ መሰረተ ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ወቅቱን የዋጀና የሃገራችንን ዲጂታል ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት ረቂቅ አዋጁን የሚያዳብሩ ሃሳቦች እና የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
የዛሬዉ የዉይይት መድረክ በሃገራችን የሚገኙና ወሳኝ መሰረተ ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማትን በማወያየት ግብአት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ ሁለተኛዉ መድረክ ነው።