ኢመደአ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ስልጠና ሰጠ
ኢመደአ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ስልጠና ሰጠ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ጉዳዮች በዛሬዉ ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ስልጠና ሰጠ።
በመድረኩ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢፌደሬ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዉጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ዲማ ነገዎ አሁን ባለንበት በኢንፎርሜሽና ቴክኖሎጂ ዘመን የሳይበር ደህንነት ጉዳይን በቸልታ ማለፍ የማንችልበት ወቅት ላይ መሆናችንን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለዉጡን ተከትሎ ለዲጂታል ሽግግር ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ተከትሎ የዲጂታል መሰረተ ልማት መስፋፋትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ማደጉን ያነሱት የተከበሩ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ይህ ሁኔታም የሳይበር ጥቃት እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመዋል።
የሳይበር ጥቃቶች መጨመር በኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ማህበራዊ መስተጋብርና ፖሊቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ እና እንደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ተጽዕኖዉ እያደገ የመጣዉን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል አንዱ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማደግ በመሆኑ ወደ መራጮች በምንሄድበት ጊዜ ስለጉዳዩ ማሳወቅ እንደሚገባ የተከበሩ ዶ/ር ዲማ አሳስበዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ዳንኤል ጉታ በበኩላቸዉ በአለም ዙሪያ የተከሰቱት የሳይበር ጥቃቶች በሀገር ደህንነት፣ በኢኮኖሚ መረጋጋት እና በዲሞክራሲያዊ ለዉጦች ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖዎች ከመቸዉም ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሳይበር ደህንነት አቅማችንን የሚያጠናክሩ እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ደህንነት የሚያረጋግጡ የህግ ማዕቀፎችን በመቅረጽ ረገድ የበኩላቸዉን አስተዋጽዎ እንዲያደርጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
እያደገ የመጣዉን የጥቃት መጠን ለመከላከል በማህበረሰቡ ላይ ተከታታይነት ያለዉ የግንዛቤ ፈጠራ ስራን መስራት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አቶ ዳንኤል የማህበረሰባችንን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና በማሳደግ ረገድ በተቋማችን እየሰራቸዉ ካሉ ስራዎች ባሻገር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካላቸዉ ተሰሚነት አንጻር የማህበረሰቡን ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ያላቸዉ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በመንግስት ተቋማት፣ በግሉ ሴክተር እና በአለም አቀፍ አጋሮች መካከል ትብብርን እና ቅንጅትን የሚጠይቅ በመሆኑ ስለስጋቶች፣ ተጋላጭነቶች እና ምርጥ ተሞክሮዎች ከአጋር አካላት ጋር መረጃ መጋራት የሳይበር አደጋዎችን የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅማችንን ልናሳድግ እንደሚገባ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።
የሳይበር ደህንነት ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ትኩረት የሚሻ ተለዋዋጭ እና ውስብስብ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የጉዳዩን አሳሳቢነት በዉል በመረዳት ጊዜዉን የዋጁ የወደፊቱን ታሳቢ ያደረጉ አዋጆች፣ ደንቦችንና ሌሎች የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።