የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ተግባር ላይ እንዲውል የሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አሳለፈ
የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ተግባር ላይ እንዲውል የሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አሳለፈ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 20/2016 ዓ/ም ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም የሳይበር ደህንነት ረቂቅ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ነባሩ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ለበርካታ አመታት በስራ ላይ የቆየ በመሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያስፈልጋቸው አዳዲስ ዓለም አለምቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሃገራዊ የሳይበር ደህንነትጉዳዮች በዘርፉ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ የፈጠሩ በመሆኑ፤ የግል እና የመንግስት ቅንጅታዊ እና የትብብር አሰራር በግልጽ ማስቀመጥ በማስፈለጉ እና ሌሎችም ዋና ዋና የትኩረት መስኮችን ያካተተ ግልጽ የአፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ዘዴ ያለው ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ በፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባ በሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ በዚህም የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስተዳደሩ እንደ የስልጣናቸው አዋጁን የሚያስፈጽሙበት ዝርዝር ህግ የማውጣት ውክልና በግልፅ ባልሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ህግ የማውጣት ውክልና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለአስተዳደሩ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
በተመሳሳይ ብሄራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሀገራት ከጥቃቅን የመዝናኛ እና የመገልገያ ዘዴዎች እስከ ብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ላሉ ቁልፍ ጉዳዮች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሀገራችንም ቴክኖሎጂውን በይበልጥ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ለማዋልና የሀገር ደህንነትን በማስጠበቅ በዘርፉ ተወዳዳሪ አቅምን ለመፍጠር ተቋም ከማቋቋም ጀምሮ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ቀሪ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባታል። የተጀመረውን ለማስቀጠል፣ ዘርፉን ለማሳደግ፣ መንግስት በዘርፉ ሊደርስ የፈለገበትን ግብ ለማመላከት እና ዘርፉ የሚገራበትን አቅጣጫ ለማሳየት በሚረዳ መልኩ ብሄራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱ በፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶች ታክለውበት ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡