የጋራ ሀገርን ለመገንባት የጋራ ትርክት መገንባትና የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ
የጋራ ሀገርን ለመገንባት የጋራ ትርክት መገንባትና የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ
የጋራ ሀገርን ለመገንባት የጋራ ትርክት መገንባትና የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ በዚህ ረገድ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል፣ ቋንቋና ወግ እንዲያድግና በብዝሃነት መሃል ያለው አብሮነትና አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ ለጋራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መሀመድ እድሪስ፣ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ (ዶ/ር) ከይረዲን ተዘራ ተገኝተዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፤ ብዝኃነት ለሺሕ ዘመናት የኖረ የሀገራችን ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ነባራዊ መልክና ቀለም መሆኑንና የብዝኃነቱ ባለቤት ደግሞ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል መከበሩ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቱ የበለጠ እንዲጠናከር ማድረጉንና ይህም የጋራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በማጠቃለያ መልዕክታቸው የክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “መደመር” መጽሐፍን ዋቢ በማድረግ እንደገለጹት፤ “የሀገራችን ብሔሮች እጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጅ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉዓላዊ ሃገር ሆነን፤ የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም፡፡ ሀገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው” በማለት የገለጹትን ሁላችንም በህብር ለሀገራዊ መግባባትና አንድነት እንስራ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በበዓሉ ላይ በጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተጻፈው “የትርክት ዕዳና በረከት” መጽሐፍ ላይ ጸሐፊው በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ በተለይም ከ1966 ዓ.ም በኋላ በርካታ አለመግባባቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ “መጽሐፉ ከተጻፈባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው እነዚህን አለመግባባቶች በውይይት መፍታት የሚቻልበት እድል መኖሩን ለማመለካት ነው” ብለዋል፡፡
የመጽሐፉ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከውይይት ይልቅ ጠመንጃ መርጠው ጫካ የገቡ ኃይሎች የፈጠሩትን ቀውስ የሚያሳይና ይሁን እንጅ ችግሩን በዚያ መንገድ መፍታት የማይቻልና መፍትሔው ቁጭ ብሎ መነጋጋር መሆኑን ለማመለከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሦስተኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ኢትዮጵያ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብቻ ሳይሆን ስልጣኔም ብዝሀነት ያላት ሀገር መሆኗንና አለመግባባቶችን ለመፍታት እነዚህን ስልጣኔዎች ማወቅና መጠቀም እንደሚገባ የሚመክር ሲሆን፤ አራተኛው ምእራፍ ደግሞ አለመግባባቶችን ለመፍታት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ያመጡት የመደመር መንገድ ከዚህ ቀደም ከሞከርናቸው መንገዶች የተለየ ብቻ ሳይሆን ሀገር በቀል የሆነና የሀገራችንን ችግሮች በውል የተረዳ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግረዋ፡፡
የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት የጋራ ሀገር ከመገንባት አኳያ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ የገለጹት ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማስከበር ለጠናካራና የጋራ ሀገር መንግስት ግንባታ እየተጫወተ የሚገኘውን ቁልፍ ሚና አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡