ኢመደአ እና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

በተቋማቱ መካከል የተፈረመዉ የመግባቢያ ስምምነት “የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እና የኢንፎርሜሽን ደህንነት የቴክኒክ ድጋፍ” የሚል ጥቅል ማዕቀፍ ያለው ሲሆን፤ ይህም በዋናነት የስደት ተመላሾች እና ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምን የተመለከተ መረጃን (የመረጃ ቋት፣ የመረጃ ማጋራት ሂደት፣ እና የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂን) ከሳይበር ጥቃት የመጠበቅና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ ፈርመዋል፡፡

በዉል ስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት ኢመደአ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚገነባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራዎች እና የመረጃ ቋቶች የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የመረጃ ደህንነትን ከመጠበቅ አኳያ መረጃው ሲቀመጥም ሆነ በስርጭት ሂደት የትኛውም አይነት የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ስራ መስራት እንደሚገባ ያነሱት ወ/ሮ ትዕግስት፤ ለዚህም ደህንነቱ የተረጋገጥ ቴክኖሎጂ መጠቀም፤ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስርአት መዘርጋት፣ እንዲሁም የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊናው የጎለበተ የሰው ሃይል መገንባት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸዉ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለዜጎች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ አጠቃላይ አሰራሩን ዲጂታላይዝ ማድረግና ደህንነቱን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑ ጠቁመው፤ ለዚህም የመግባቢያ ስምምነቱ አስቻይ ሚናን ይጫወታል ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ በበኩላቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሰራሩን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ሚኒስቴር መ/ቤታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የስደተኞችና የስደት ተመላሾች መረጃ መለዋወጫ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስበት ተገቢዉን ድጋፍ የማድረግ፣ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ስልጠና የመስጠት፣ የመረጃ መለዋወጫ መሰረተ ልማቱ ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ዝርጋታ ላይ ሙያዊ ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የመረጃ መለዋወጫ መሰረተ ልማቱ የሳይበር ጥቃት እንዳይከሰትበት ቀጣይነት ያለዉ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ይሆናል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ካደረገው የመግባቢያ ስምምነት በተጨማሪ፤ “የስደት ተመላሾች እና ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምን የተመለከተ መረጃ የሚያመነጩ ተቋማት የመረጃ መጋራት ፕሮቶኮል” በሚል ርዕስ ከተለያዩ ስምንት የፌዴራል ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት አድርጓል፡፡

Asset Publisher


የቅርብ ዜናዎች