የ14ኛ ዙር 20/80 እና 3ኛ ዙር 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጣት ሥነ ስርአት ተከናወነ
የ14ኛ ዙር 20/80 እና 3ኛ ዙር 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጣት ሥነ ስርአት ተከናወነ
የ14ኛ ዙር 20/80 እና 3ኛ ዙር 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጣት ሥነ ስርአት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተከናወነ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ለጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጫ የሚሆን ሲስተም በማበልጸግ እና በሚመለከታቸው አካላት በማስፈተሽ ለዚህ የእጣ ማውጫ መርሃ ግብር አገልግሎት ላይ አውሏል፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ የእጣ ማውጣት ሥነ ስርአቱን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ኢመደአ በመንግስት በተሰጠው ሀገራዊ ሀላፊነት መሰረት ከዚህ ቀደም በአንዳንድ አካላት የተፈጠረዉን ስህተት በፍጹም በማይደግም መልኩ በንጹህ ልብ፣ በንጹህ አእምሮ እና በንጹህ እጅ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ሚስጥር ሲስተሙን አልምቷል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በኢመደአ የለማዉ የእጣ ማዉጫ ሶፍትዌር ወደ አገልግሎት ከመግባቱ አስቀድሞ በተለያየ ደረጃ በሚመለከታቸዉ አካላት የደህንነት ፍተሻዎች እንደተደረገለት ገልጸዋል። ከደህንነት ፍተሻዉ በኋላም በዛሬዉ ዕለት የሚመለከታቸዉ የመንግስት ከፍተኛ ሀለፊዎች፣ የባለድርሻ አካላትና የቤት ቆጣቢዎችን ታዛቢ ባደረገ መልኩ ሲስተሙን በመጠቀም እጣ ማዉጣት ተችሏልም ሲሉ አብራርተዋል።
ላለፉት ጥቂት አመታት ከሌላችሁ ላይ በመቆጠብ የቤት ባለቤት ለመሆን ስትጠባበቁ ለነበራችሁና በዛሬዉ እለት ባለ እድል ለሆናቸዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ሲሉም አቶ ሰለሞን ሶካ ለባለ እድለኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡