የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (ETEX 2025) ሀገሪቱ የፈጠረችዉን የቴክኖሎጂ አቅም ለዓለም የምታሳይበት መድረክ እንደሆነ ተገለጸ
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (ETEX 2025) ሀገሪቱ የፈጠረችዉን የቴክኖሎጂ አቅም ለዓለም የምታሳይበት መድረክ እንደሆነ ተገለጸ
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (Ethiopian Technology Expo - ETEX 2025) ሀገሪቱ የፈጠረችዉን የቴክኖሎጂ አቅም ለዓለም የምታሳይበት ትልቅ መድረክ እንደሆነ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
ኤክስፖውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዛሬ እለት ተሰጥቷል።
ከግንቦት 8 እስከ 10/2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ፤ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄደው ኤክስፖ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ታሪካዊ ዳራ፣ አሁን የደረስንበት ደረጃ እና በቀጣይ ልንደርስበት ያለምነውን ግብ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳየትና የአፍሪካ የቴክኖሎጂ የስሕበት ማዕከል ለመሆን ትልቅ መደላድል የሚፈጥር ነው፡፡
ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን ይህንን ዓለም አቀፍ ሁነት ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬት አዎንታዊ ሚናን መጫወት በሚችልበት አግባብ ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ድኤታው በዚሁ ወቅት እንደገለጹ፤ መገናኛ ብዙሃን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ እያከናወነች ስላለው ተግባራት ጥልቅ መረጃ ማድረስና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ እንደተናገሩት ኤክስፖው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ለመሆኑ ሁነኛ መሳየ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ይህንን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬቶችና ቀጣይ ትልሞች በአግባቡ መናገር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (ETEX 2025) ከግንቦት 8 እስከ 10/2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ፤ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡