ኢመደአ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የሳይበር ደህንነት "የሰመር ካምፕ" ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን 62 ታዳጊ ወጣቶችን አስመረቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ2014 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የሳይበር ደህንነት "የሰመር ካምፕ" ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን 62 ታዳጊ ወጣቶችን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተጋ እንግዶች እና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም አስመረቀ፡፡

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለተመራቂዎቹ ሰርተፊኬት የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት “መጀመር ከባድ ቢሆንም ማዝለቅም በራሱ ፈታኝ ጉዞ ነውና ይህንን ተነሳሽነት ወስደው ወጣቶቹን ለምረቃ  ላበቁ ኢመደአን ጨምሮ የተለያዩ ተሳታፊ ተቋማት እና ባለሃብቶች ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ አያይዘው እንደገለጹት የሳይበር ምህዳር ከፍተኛ የሃብት ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው ማልማት እና መጠቀም የሁሉም አካል ሚና በመሆኑ መንግስትም ለምህዳሩ አመቺ የሆኑ መደላደል ለመፍጠር ሚንስትር መስሪያ ቤታቸውን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት የህግ እና ፖሊሲዎችን በማውጣት እንዲሁም የግል ባለሃብቶችም ዘርፉን በአቅማቸው እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ሚንስትሯ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት  ሌሎች የዓለም ሃገራት በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ለአፍሪካ የሚሰጡት ግምት ዝቅተኛ መሆኑን ተረድተው ሀገራቸውን ብሎም አፍሪካ የማስጠራት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት  ሀገራችን ላቀደችው የዲጂታል ኢኮኖሚ እና የዲጂታላይዜሽን ስርዓት ግንባታ ላይ አይበገሬና የማይደፈር የሳይበር ደህንነት መፍጠር ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን ለመደገፍ የተመራቂዎቹ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ መንግስት ለታለንት ልማት ማበልጸጊያ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ሚኒስትሩ የቡራዩ ልዩ ተሰጥዖ ማበልጸጊያ ማዕከል አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው ሌሎች መሰል ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ ለተመራቂዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን “የዛሬ ተመራቂዎች የነገዋ ብሩህ ኢትዮጵያ አመላካቾችና ተስፋዎች ናችሁ” ብለዋል፡፡ ኢመደአ ዓለም አቀፋዊ በሆነዉ የሳይበር ደህንነት ኢንዱስትሪ ዉስጥ የሚሰራ ተቋም በመሆኑ ስራዎችን ሲሰራ የአሁኑን እና የነገዉን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን ሲሆን ከዘመኑ ጋር እኩል መጓዝ የምትችልና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር  ልዩ ተሰጥዎችን በአግባቡ ማቀብ፣ ማልማትና ፍሬ እንዲያፈሩ ማድረግ አስተዳደሩ በትኩረት የሚሰራበት ዘርፍ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡  

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የወጣቶችን እምቅ አቅም እና ልዩ ችሎታ ለሀገር ልማትና እድገት ማሳለጫ እንዲዉል የልዩ ተሰጥዎች ማበልጸጊያ ማዕከላትን መገንባትና ተሰጥዎችን በተገቢዉ መልኩ ማቆየት፣ ማዳበር እና ማበልጸግ  ያላሰለሰ ጥረትን እና ያልተቋረጠ ክትትልን ይጠይቃል ብለዋል ። ኢመደአ በተለያዩ ባለልዩ ተሰጥዖ ወጣቶች የለሙ የሳይበር ደህንነት ምርቶች በኢንዳስትሪ ደረጃ ተመርተዉ የሀገር ሃብት እንዲሆኑና በዘርፉ የስራ እድል እንዲፈጠር ከባለ ሃብቶች ጋር የማገናኘትና የማስተሳሰር ስራዎች እየሰራ ይገኛል። እነዚህ የፈጠራ ዉጤቶች ለሀገር ልማት እና እድገት አቅም እንዳይሆኑ ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ የአሰራር ስርዓቶች፣ ደንቦች፣ ፖሊሲዎችና አዋጆችም ካሉ በመከለስ ጀማሪ የሰራ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚያበረታታና የሚደግፍ የፖሊሲ አማራጮችን በመፍጠር አዳዲስ ፈጠራዎችን  መደገፍና ማበርታታት ወሳኝ መሆኑንንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በማጠቃለያ መልዕክታቸው በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸዉን ታዳጊዎች አቅማቸዉን በማጎልበት እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ከኢመደአ ጋር በመሆን የማማከር፣ የመደገፍ እና የማብቃት ስራ ለሰሩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢመደአ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በመርሃ ግብሩ ለተገኙ እንግዶች የኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል ላማ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የማዕከሉ ዋና ዓላማ ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ስብስብ መፍጠር እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መረሃ ግብሩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የሞሃን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃርሽ ኮታሪ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የሳይበር ኢንዱስትሪ ዘርፍ አዋጭና ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆኑን በመጥቀስ ባለሃብቶች በዘርፉ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያውሉ አበረታተዋል፡፡

በዛሬው እለት ለምረቃ የበቁት ባለልዩ ተሰጥዖ ታዳጊ ወጣቶች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ሲሆን በሳይበር ሴኪሪቲ፡ ዌብ ሎፕመንት፣ ኤሮስፔስ እና ኢምቤድድ ሲስተም ላይ ሲሰለጠኑ ቆይተዋል። በስልጠና ቆይታቸውም ከ25 በላይ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት የቻሉ ሲሆን ይህንኑ የፈጠራ ሥራዎቻቸው ለአንድ ሳምንት ያህል በሳይንስ ሙዚየም ለሕዝብ ሲያስጎበኙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡