5ኛው የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 1/2017 እስከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ድረስ ይከበራል
Nested Applications
Asset Publisher
Asset Publisher
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ከጥቅምት 1-30/2017 ዓ.ም ድረስ የሚከበረውን 5ኛውን ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው 5ኛው የሳይበር ደህንነት ወር “የቁልፍ መሰረተ-ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አዘጋጅነት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡ የጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነት ወር በመባል የሚታወቅ ሲሆን በወሩ በርካታ ሃገራት የዜጎቻቸውንና የተቋሞቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊናን ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በሃገራችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እና ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ዳይሬክተሯ ጠቁመው፣ የሳይበር ደህንነት ወር የተቋማትን እና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና በማጎልበት ለሳይበር ደህንነት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡና እራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንዲችሉ የሚያግዙ የተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚካሄዱበት ወር እንደሆነ ገልጸዋል።
5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የመክፈቻ ፕሮግራም ጥቅምት 1/2017 ዓ/ም በሳይንስ ሙዚየም የሚከፈት ሲሆን፤ በእለቱ “የቁልፍ-መሰረተ ልማት የሳይበር ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ እንደሚካሄድ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ከውይይቱ ባሻገር በእለቱ የከሰአት ፕሮግራም ከቀኑ 8፡00 ሰአት ጀምሮ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የሚካፈሉበት ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዘ አጭር የተሳታፊዎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ መለካት የሚያስችል ውድድር ይካሄዳል፡፡
በሁለተኛው ሳምንት ፕሮግራም ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም አዲስ በተሻሻለውና በ2016 ዓ/ም ጸድቆ ተግባር ላይ በዋለው የሀገራችን የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ዙሪያ ምክክር የሚደረግ ሲሆን፤ በሦስተኛው ሳምንት ፕሮግራም ጥቅምት 21/2017 ዓ.ም የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለሳይበር ደህንነት በሚጫወተው ሚና ዙሪያ ከሃይስኩል እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ወጣቶችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያማከለ የቨርቹዋል ዉይይት የሚካሄድ ይሆናል።
በአራተኛው ፕሮግራም ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም በስማርት ሲቲ ጉዞ ላይ የሳይበር ደህንነትና የዲጂታል መታወቂያ ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤ የሳይበር ወሩ የማጠቃለያ ፕሮግራም ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጸዋል፡፡
ከላይ ከሚዘጋጁት ዋና ዋና መርሃ ግብሮች ባሻገር ወሩን ሙሉ የማህበረሰቡንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ አዝናኝና አስተማሪ በሆነ መልኩ ማህበረሰባዊ የሳይበር ደህንነት ንቅናቄ ስራ እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
ኢመደአ የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት ዋና ባለድርሻ ሆኖ የንቃተ ህሊና መስጫ መርሃ ግብሮችን የሚያከናውን ሲሆን፤ በተመሳሳይ ተቋማት የሳይበር ደህንነት የማረጋገጥ ሥራ የጋራ ሃላፊነት መሆኑን በመረዳት የሰራተኞቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ ወሩን እንዲያከብሩ ዋና ዳይሬክተሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሳይበር ደህንነት ወር በአለም አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል፡፡