የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ስርዓትን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ስርዓትን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም፡- የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ስርዓትን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችል የውይይት መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሄደ፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የበለጸገው የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ አስተዳደር ስርዓት (Electronic Invoice Management System) የሀገሪቱን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት የሚያዘምንና ከማንዋል ደረሰኝ ጋር ተያይዞ በግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱና በግብር ከፋዩ መካከል ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን የሚያስቀር እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ የታክስ አስተዳደሩን ውጤታማ ሊያደርጉ ከሚችሉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች አካል የሆነው የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ስርአት ወደ ተግባር ለማስገባት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በማውጣት በመተግበር ላይ መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሯ ስትራቴጂው ትግበራ ከሚከናወንባቸው ተቋማት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የገቢው ዘርፍ እንደመሆኑ ለትግበራው የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በራስ አቅም ቴክኖሎጂዎችን በማልማት የዲጂታል ግብይት የአገልግሎት አሰጣጥን በማስፋት የስነ-ምግባር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ስርዓትን ወደ ስራ ለማስገባት የሙከራ ትግበራ ተደርጎ ውጤታማነቱ መረጋገጡን የገለጹት ሚኒስትሯ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ከማንዋል ደረሰኝ ጋር ተያይዞ በግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱና በግብር ከፋዩ መካከል ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ያስቀራል ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተቀናጀ ታክስ አስተዳደር ስርዓት ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍፁም ወሰኔ ቴክኖሎጂውን የተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ከክብርት ሚኒስትሯ ጋር በመሆን ምላሽ ሰጥተዋል።