ኢመደአ የ2017 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ፕሮግራም በይፋ አስጀመረ
ኢመደአ የ2017 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ፕሮግራም በይፋ አስጀመረ
አዲስ አበባ፤ሀምሌ 25/2017፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተደራሽ የሆነ ብሄራዊ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ምልመላ በማካሄድ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የ2017 በጀት አመት ፕሮግራም የሰመር ካምፕ በአዲስ አበባ በይፋ አስጀመረ።
በዚህ ፕሮግራም የተሳተፉ ባለልዩ ተሰጥዎ ታዳጊዎች በተለያዩ አካባቢዎች ከተመዘገቡ ስምንት ሺህ (8,000) ተመዝጋቢዎች መካከል በየደረጃው የተሰጡ የተለያዩ ፈተናዎችን ያለፉ ሰባት መቶ ሰማንያ አራት (784) ባለተሰጥዎች መካከል 700 ባለልዩ ተሰጥዎችን የያዘ ነዉ።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ይህ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮግራም የባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ ወጣቶችን ሕልምን ከተጨባጭ እድል ጋር የሚያገናኝ እንዲሁም የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ሂደት ዉስጥ የማይተካ ሚና የሚጫወቱ የሳይበር ሰራዊቶች የማፍራት እንቅስቃሴ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።
የሰመር ካምፕ ተሳታፊዎች በቆይታቸዉ በእውቀት፣ በአስተሳሰብ እና በሥነ ምግባር በመታነጽ የሀገራችን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ መደገፍ እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።
ባለፉት ሦስት አመታት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረዉን ፕሮግራም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ 84 ባለልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎችን በመያዝ በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት ወ/ሮ ትዕግስት በቀጣይም ወደሌሎች የሀገራችን ከተሞች በማስፋት የሳይበር ታለንት ልማት ሥራ ሀገራዊ መልክ እንዲይዝ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ለዚህ እቅድ ስኬት ኢመደአ ከሚመለከታቸው ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከድር ኢብራሂም በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲያቸዉ ከኢመደአ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራ መቆየቱን ጠቁመው በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት በሳይበር ታለንት ልማት ዘርፍ ምሳሌ የሚሆን ስራ በጋራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የ2017 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ጎን ለጎን በዚህ ፕሮግራም ተሳታፊ የሆኑ ታዳጊዎች ከተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናዉነዋል።