ኢመደአ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከሁለት ባንኮች ጋር የደራሽ የክፍያ ስርዓትን ለመጠቀም የሶስትዮሽ የዉል ስምምነት ተፈራረመ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከአማራ ባንክና ከጸሃይ ባንክ ጋር የደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርምን ለመጠቀም የሚያስችል የሶስትዮሽ የዉል ስምምነት ተፈራረመ።

በዉል ስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሀሚድ እንደገለጹት በዛሬው እለት ከገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም ከአማራ ባንክና ከጸሀይ ባንክ ጋር የፈረምናቸዉ ስምምነቶች በደራሽ ፕላትፎርም ላይ የሚጠቀሙ የባንኮችን ቁጥር ወደ 21 ከፍ የሚያደርገዉ ነው ብለዋል።

በፕላትፎርሙ የሚጠቀሙ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር እና የገንዘብ ዝዉዉር በየጊዜዉ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ እስከ የካቲት 18/2016 ብቻ በፕላትፎርሙ አማካኝነት 59 ቢሊዮን ብር ገደማ ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ታክስ መሰብሰቡን ጠቁመዋል። ይህም ፕላትፎርሙ ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን የሚያሳይ ነዉ ብለዋል።

በዛሬዉ እለት የተፈራረምናቸዉ የዉል ስምምነቶችም ፕላትፎርሙን በቀጣይነት እንድናለማና ለሃገራችን የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2025 ስኬት ብቻ ሳይሆን የግብር መጭበርበርን የሚቀንስ እንዲሁም የግብር ከፋዩን እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን አንስተዋል።

የደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርም አሁን ከሚሰጠው ግልጋሎት በተሻለ ደረጃዉን ከፍ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘዉ በደራሽ የተቀናጀ ፕላትፎርም አማካኝነት ኢመደአ እንደ ተቋም ምንም አይነት ክፍያዎችን ሳያስከፍል ላለፉት 6 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ በቀጣይ ግን የደራሽን የተቀናጀ የክፍያ ስርዓት ኦፕሬሽናል ወጪዎቹን ለመሸፈንና ራሱን ለማዘመን ተመጣጣኝ ክፍያ ማስከፈል የሚጀምር መሆኑን ጠቁመዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸዉ ሚኒስቴር መስሪያቤታቸዉ ዲጂታላይዝድ የሆነ የታክስ ስርዓትን በመዘርጋት ከፍተኛ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዉ እስከ ጥር 2016 ዓ/ም ባለዉ ጊዜ ብቻ 53 በመቶ የሚሆነዉ ታክስ በኤሌክትሮኒክስ ታክስ ስርዓቶች መከናወኑን አንስተዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸዉ እንደ ደራሽ ያሉ ዲጂታል የሆኑ የታክስ ስርዓቶች መጠቀማቸዉ፣ ጊዜን በመቆጠብና እንግልት በመቀነስ የግብር ከፋዩን ማህበረሰብ የአገልግሎት እርካታ ማላቅ መቻሉን በዉል ስምምነቱ ወቅት ጠቁመዋል።

የደራሽ የተቀናጀ የክፍያ ስርዓት በኢመደአ ለምቶ በ2010 ዓ/ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በቁጥር 10 የሚሆኑ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን በመያዝ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ21 በላይ የሚሆኑ ባንኮች፣ ቴሌ ብር እና 19 ከሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር እየሰራ ያለ ፕላትፎርም ነዉ።