በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት በሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሪን በሚያሳጣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 30 ግለሠቦችና የተለያዩ መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

በአዲስ አበባ፣ ሸገር ከተማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሃዋሳ እና ጂማ ከተሞች በተደረገ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከ73 በላይ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሣሪያዎች እና 30 ተጠርጣሪ ግለሠቦች እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሙያዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ላለፉት ሦስት ወራት በቴሌኮም ማጨበርበር ወንጀል ተዋንያን ላይ ጥብቅና ሚስጥራዊ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ተቋማቱ ግኝቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን በላኩት የጋራ መገለጫ እንዳስታወቁትም፤ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የግለሠብ ቤቶችንና ግቢዎችን በመከራየት የማጭበርበሪያ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ወንጀሉን ሢሰሩ ቆይተዋል፡፡

ለዚሁ ሕገ ወጥ ተግባር ሲውሉ የነበሩ ከ200 ሺህ በላይ የሳፋሪኮም እና ኢትዮቴሌኮም ሲም ካርዶች መያዛቸው በመግለጫዉ ተመልክቷል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉ የማጭበርበሪያ ጌትዌይ መካከልም በአንድ ጊዜ 127 የኢትዮቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም ሲም ካርድ መያዝ የሚችል መሣሪያ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸሙት የማጭበርበር ድርጊቶች ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣ የጠቆመው መግለጫው፤ ኢትዮቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በዚህ ሕገ ወጥ ተግባር የተነሳ ማጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሕገ ወጥ ድርጊቱ በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት የሚፈጥርም መሆኑን ያመለከተው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የጋራ መግለጫ፤ በማጭበርበሪያ መሣሪያዎች የተነሳ በቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ጠቁሟል፡፡

መሣሪያዎቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆን፤ ከኢትዮቴሌኮም ይሁን ከሳፋሪኮም ምንም እውቅና የሌላቸው ነገር ግን ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት የማጭበርበሪያ ጌትዌይ ለደንበኞች የሚያቀርቡ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በማጭበርበሪያ መሣሪያው የሚፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት ሀገራዊ ጥቅምን ከማሳጣትና የደኅንነት ሥጋት ከመደቀን ባሻገር የቴሌኮም ደንበኞች በሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ ጥራት ያለው የኔትዎርክ አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን፤ በዚህም ደንበኞች በቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት እንዲማረሩና ሀገራዊ መረጋጋት እንዳይኖር አስተዋጽዖ ማበርከቱን መግለጫው አስታውቋል፡፡

በማጭበርበር ወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ ግለሠቦች ሰፊ ኔትዎርክ ያላቸው ሲሆን ከአለማቀፍ ተዋንያን እስከ ሀገር ውስጥ ቤት አከራይ ድረስ ትስስር አላቸው ያለው የተቋማቱ የጋራ መግለጫ፤ የማጭበርበሪያ መሣሪያ ከጎረቤት ሀገራት በድንበር በኩል እስከ መሀል ከተማ ድረስ የሚቀባበሉ ደላሎች፣ በርካታ የኢትዮቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ሲም ካርድ እና ሞባይል ካርድ ለእነዚህ አጭበርባሪዎች የሚያደርሱ ተባባሪ ወንጀለኞች እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡ በተለይ ተጠርጣሪዎች መቀመጫቸውን ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራት ካደረጉ ዜጎች ጋር በመመሳጠር እና ተቀጥረው በመሥራት ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደተደረሰባቸው መግለጫው ጠቁሟል።

እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የጋራ መግለጫ፤ በኦፕሬሽኑ በተያዙት መሣሪያዎች እና በተጠርጣሪዎች ላይ ቀጣይ ምርመራ ይደረጋል፡፡ ይህንንም በተከታታይ ለሕዝብ የማሳወቅ ሥራ ይከናወናል፡፡ ሁሉም አካላት በሀገር፣ በዜጎች እና በተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱት እነዚህና ሌሎችም መሰል ወንጀሎች ከጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት እይታ እንደማይሰወሩ ተገንዝበው ከሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል መግለጫው።

ኅብረተሰቡም የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶች ከሚያደርሱት የኢኮኖሚ ኪሳራ በተጨማሪ በሀገር ደኅንነት ላይ የሚያደርሱትን አደጋ በመገንዘብ በተመሳሳይ ወንጀል የሚሳተፉ ግለሠቦችና ተቋማት መኖራቸውን ጥርጣሬ ሲያድርበት በተለይ በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታና የሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማውን በማቅረብ ሕገወጦችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

Asset Publisher


የቅርብ ዜናዎች