ኢመደአ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መስራት በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
ኢመደአ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መስራት በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መስራት በሚችሉባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ የተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙነት ዉይይት አደረጉ።
ከውይይቱ ባሻገር በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና መ/ቤት በመገኘት ጉብኝት አካሂዷል፡፡
በዉይይቱ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሰተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ኢመደአ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን፣ የመረጃ የበላይነትን እና የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ስላለዉ ስራ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ኢመደአ ከዚህ ቀደም ከፌደራል ፖሊስ ጋር በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአሰራር ስርአቱን ለማዘመን እየሰራቸዉ ባሉ ስራዎች ኢመደአ ባለዉ አቅም ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸዉ በአሁኑ ሰዓት ከአካላዊ ወንጀሎች ባሻገር በሳይበሩ ስነ ምህዳር ላይ የሚሰነዘሩ ወንጀሎች እያደጉ መምጣታቸዉንና ይህንን በብቃት ከመከላከል አኳያ ከኢመደአ ጋር ከዚህ ቀደም ከነበረዉ በላቀ መልኩ ትብብርና አጋርነት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በተለይ በሀገራችን የዲጂታል ተጠቃሚዎች ቁጥር በጨመሩ እንዲሁም የሳይበር ወንጀሎች እና የሚፈጽሙትም ወንጀል በመጠንም ይሁን በውስብስብነት እጅግ እያደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ላይ እንደ መረጃና ጸጥታ ተቋም እጅ ለዕጅ ተያይዞ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጠቁመዋል።
ከዚህ አኳያ ኢመደአ የፈጠራቸዉ ሀገራዊ አቅሞች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ እነዚህ አቅሞች በጸጥታ ስራ ላይ ያላቸዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በተቋማቱ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ላይ በመድረስ ስራዎች እንዳይደጋገሙ፣ የመንግስት ሀብትን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም በተቋማቱ መካከል ያለ አቅምን አስተባብሮ ለመሄድ በሚያስችል መልኩ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዉይይቱ ባሻገር የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች በተቋሙ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተዟዙረዉ ጎብኝተዋል።