ለ60 ሚሊየን ዜጎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ግንዛቤ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ተሰጥቷል - አቶ ሰለሞን ሶካ፡ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር
ለ60 ሚሊየን ዜጎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ግንዛቤ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ተሰጥቷል - አቶ ሰለሞን ሶካ፡ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር
በ4ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር 60 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ግንዛቤ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች መሰጠቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡ “አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሃገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1 – 30 /2016 ዓ.ም የተካሄደውን 4ኛውን ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በስኬት መጠናቀቅ አስመልክቶ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በ4ኛው የሳይበር ደህንነት ወር ለማሳካት በእቅድ ከተያዙት አላማዎች መካከል በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የነገዉን ትዉልድ ያተኮሩ የግንዛቤ ስራዎችን ማከናወን ፣ ተቋማት ይህን አለማቀፍና ሃገራዊ ሁነት በራሳቸዉ አዉድ ወስደዉ ተቋማዊ ንቅናቄን እንዲያደርጉ መደገፍ፣ የሳይበር ማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ማጎልበት፣ የተቋማት የሳይበር ደህንነት ዝግጁነት ማሻሻል፣ የሳይበር ደህንነት ጥናትና ምርምሮችን ማበረታታት፣ እንዲሁም በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ መስክ የተሰማሩትን የግሉን ዘርፍ ማነቃቃት እንደበነር አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል፡፡
4ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ከተነሳለት አላማ አኳያ የሳይበር ማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማጎልበት የሚያስችሉ ከወትሮ የተለዩ ስልቶችን በማካተት በአዝናኝና አስተማሪ ፊልም “ሥውር ውጊያ” ፊልም በመጀመር እንዲሁም ጥናትና ምርምር ላይ መሰረት ያደረጉ ተጨባጭ ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ቁመናን የፈተሹና ቀጣይ ትልማችንን የነደፍንበትና ተቋማትን በሰፊዉ ያሳተፈ ነበር ሲሉ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም እንደገለጹት በዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር በተካሄዱ ኮንፈረንሶችና የአዉደ ርዕይ መርሃ ግብሮች ከ150 በላይ ተቋማት የተዉጣጡ ከአምስት ሺ (5,000) በላይ ሰዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በ4ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አራት ዋና ዋና መርሃ ግብሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ የወሩ የመክፈቻ መርሃ ግብር የነበረውና በኢመደአ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ እይታ የበቃው “ሥውር ውጊያ” የተሰኘ ፊልም፤ በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የቀረበው ሃገራዊ የሳይበር ስጋት ተጋላጭነት፤ በሦስተኛ ሳምንት ይፋ የተደረገው “ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ደረጃ” የጥናት ውጤት፣ እንዲሁም በሃገራዊ የሳይበር ደህንነት የሕግ ማዕቀፍ፣ ፖሊሲና ስታንዳርድ ዙሪያ ለክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የአይ.ሲ.ቲ ቢሮ ሃላፊዎች በቪዲዮ ኮንፍረንስ የተሰጠ የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ፤ በአራተኛውና በወሩ የመጨረሻ መርሃ ግብር የተካሄደ “ሃገራዊ የሳይበር ደህንነት የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ” በወሩ የተካሄዱ ዋና ዋና መርሃ ግብሮች መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ሶካ አብራርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በማጠቃለያ መልዕክታቸው 4ኛው ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ገልጸው፤ በተለይም ከኢመደአ በተጨማሪ ሁሉም የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት እንደ አዉዳቸዉ በመዉሰድ የሳይበር ደህንነት ንቅናቄን ማካሄድ እንዳለባቸው እና ይህን ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት መታየታቸዉ ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም 4ኛውን ሃገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ስፖንሰር በማድረግ፣ በአዉደ ርዕይ አቅራቢነት፣ በተሳታፊነት፣ በአወያይነት፣ በጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢነት፣ በሚድያ ስርጭት፣ በአዘጋጅነትና በሌሎችም በማንኛዉም ረገድ 4ኛውን የሳይበር ደህንነት ወር ስኬታማ ለማድረግ አስተዋጽዖ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።