“ብዝሀነትና እኩልነት ለሃገራዊ አንድነት ”
“ብዝሀነትና እኩልነት ለሃገራዊ አንድነት ”
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አመራር እና ሠራተኞች 18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ብዝሀነትና እኩልነት ለሃገራዊ አንድነት ” በሚል መሪ ቃል በጋራ አከበሩ፡፡
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የኢመደአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ዳዊት ለአራቱም ተቋማት አመራርና ሠራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት በዓሉ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ የሕብረ-ብሔራዊነት፣ የእኩልነት፣ የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶችን የምናጎለብትበት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ብዝሀነት በኢትዮጵያ እውነት ስለሆነ እሱን ማድነቅና መቀበል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አያይዘውም አተገባበራችን እንጂ መንግስታዊ ስርአት በራሱ ስህተት ወይም ትክክል እንደማይሆን በርካታ አገራት በተለያየ የአስተዳደር ሥርአት ውስጥ ውጤታማ መሆናቸው ማሳያ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን ለማጠናከር ፍትህና እኩልነትን ለማስፈን፣ ብዝሀነታችንን ማክበር እንዳለብን አስገንዝበው፤ ለዚህም ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ በበኩላቸው ይህ ቀን የአብሮነት ቀን መሆኑን ጠቅሰው ፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የልዩነቶቻችን ምክንያት ሳይሆኑ የውበትና የጥንካሬ መገለጫ፣ እንዲሁም የአንድነታችን አቅም ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ም/ል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብዝኀነት ሀገር በመሆኗ ሌሎች ሀገራት የሌላቸው እኛ ግን ያለን ልዩ አቅም እንደሆነ ገልጸው ብዝሀነታችን ውበታችን እንጂ የግጭት ምክንያት መሆን የለበትም ብለዋል ፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የተጋባን፣ የተጋመድን እና ትልልቅ የጋራ ታሪክ ያለን፣ አንድነታችን የተጠበቀ ሕዝቦች እንደሆንን አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርአት አተገባበር ጥንካሬዎችና ችግሮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ የመፍትሄ ሃሳቦችም ተመላክተዋል፡