ኢመደአ የሙስና ጥቆማ መቀበያ ሶፍትዌር በማልማት ለሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስረከበ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የመንግስት ተቋማት ላይ ከሕዝብ የሚቀርቡ አስተያየቶችን፣ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን እንዲሁም የሙስና ጥቆማዎችን ለመቀበል የሚያስችል ሶፍትዌር በማልማት ለፌዴራል የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስረከበ፡፡ ርክክቡን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ እና የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ፈጽመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ባስተላለፉት መልዕክት ሃገር አቀፍ የሙስና ትግል በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉንም አሳታፊ የሙስና ትግልን ማጠናከር ያስፈልጋል፤  በዋናነት ሕብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል አለብን ብለዋል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የማጋለጥ ሃላፊነት ለሕግ አካላት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ሕብረተሰቡ የሙስናን አስከፊነትና ተጽእኖውን በውል በመረዳት ለሃገር አቀፍ የሙስና ትግል የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ከመታገል አንጻር ሕብረተሰቡ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቀበያ ሶፍትዌር በማልማት ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስረክበናል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ሶፍትዌሩን አልምቶ ማስረከብ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱ በተረጋገጠ መልኩ ጠቋሚዎችና ምስክሮች የሚሰጡት መረጃ በአግባቡ ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ጥበቃ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የሶፍትዌሩ ዋና ዓላማ የሕብረተሰቡን እውነተኛ ስሜት በማድመጥ የመንግስት ተቋማትን አሰራር ውጤታማ ማድረግ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

ዜጎች በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላይ በሚያገኟቸው አገልግሎቶች ላይ ያላቸውን አስተያየት ወይም የእርካታ መጠን፣ በአገልግሎት ሂደት የሚገጥማቸው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም የሙስና ጥቆማ ሶፍትዌሩን በመጠቀም በየትኛውም ቦታ በፈለጉበት ሰአት ጥቆማ ወይም አስተያየታቸውን መስጠት እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ኢመደአ ሃገራዊ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ሂደት የሚያለማቸውን ቴክኖሎጂዎች ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት እንደሚያስታጥቅ የገለጹት አቶ ሰለሞን ሶካ ይህንን የሙስና ጥቆማ መቀበያ ሶፍትዌር ሕብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀምና ሃገራዊ የሙስና ትግሉን እንዲደግፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሃገር አቀፍ የሙስና ትግል ላይ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ማበረታታት እንደሚያስፈግ ገልጸው፤ ይህንን ከማድረግ አንጻር ኮሚሽኑ ጠቋሚዎችንና ምስክሮችን ለማስፋት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያለማው የጥቆማ መቀበያ ሶፍትዌር የሙስና ትግሉን ከማሳለጥ አንጻር በተለይም ጠቋሚዎችና ምስክሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው ካለምንም መሳቀቅና መሸማቀቅ ደህንነታቸው ተጠብቆ ጥቆማ እንዲሰጡ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ብለዋል፡፡

ሶፍትዌሩ የኮሚሽኑን ሥራ ከማቀላጠፍ አኳያ ጥቆማዎችን ለመቀበል ያወጣ የነበረውን ገንዘብና ጊዜ በማስቀረት፣ ሕብረተሰቡ ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲኖረው በማድረግ እንዲሁም ሕብረተሰቡ የሚሰጣቸውን ጥቆማዎች በቀጥታ የትኛውም ሦስተኛ ወገን ሳይነካካው ለማግኘት እንደሚረዳ ዶ/ር ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

የጥቆማ መቀበያ ሶፍትዌሩን ቴክኒካል ጉዳዮች በተመለከተ በኢመደአ የቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አለቃ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም ሶፍትዌሩ በ5 ሃገርኛ ቋንቋዎች በተጨማሪም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በየትኛውም የአለም ክፍል ላይ 24/7 (24 ሰአት 7 ቀን) አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል፡፡ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ከማሳተፍ አኳያም ለአይነ ሥውራን ዜጎች ምቹ በሆነ መልኩ በድምጽ ታግዘው አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ መሰራቱንም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ሶፍትዌሩ ከኮምፒውተር በተጨማሪ የሞባይል አፕሊኬሽንም ስለተሰራለት ሕብረተሰቡ በቀላሉ ከአፕ ስቶር  ወይም ፕሌይ ስቶር በማውረድ መጠቀም እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ሶፍትዌሩ ሦስት ዋና ዋና አገልግሎቶች እንዳሉት የገለጹት ባለሙያው እነዚህም፤ በማንኛውም የመንግስት ተቋማት ላይ የሚቀርቡ የሕዝብ አስተያየቶችን፣ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን፣ እንዲሁም የሙስና ጥቆማዎችን ለመቀበል የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ሶፍትዌሩ “የሕዝብ አስተያየት መቀበያ ሲስተም - Public Feedback System የሚል መጠሪያ ስያሜ እንዳለው የገለጹት አቶ ብርሃኑ ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል የሶፍትዌሩን ዌብሳይት አድራሻ https://epfs.gov.et በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ብለዋል፡፡