በ2015 በጀት አመት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል 23.2 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ አቶ ሰለሞን ሶካ፡ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 17/2015 ዓ/ም፡ በ2015 በጀት አመት ሃገሪቱ ላይ ሊደርሱ የነበሩ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል 23.2 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የገለጹት የአስተዳደሩን የ2015 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

በ2015 ዓ/ም በጀት አመት በሀገራችን 6‚959 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች የተፈፀሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 6,768 ምላሽ የተሰጠባቸው እና የተቀሩት 191 የጥቃት ሙከራዎች የተሳኩ ሲሆን እነዚህ የተሳኩ የሳይበር ጥቃቶች ምላሽ የሚፈልጉትን በመለየት 96.02% ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ቀሪዎቹ 3.98% የሚሆኑት በሂደት ላይ እንዳሉ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጸዋል፡፡

የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ የማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነትን መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸዉን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ያደረጉ ሲሆን፤ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፤ ሚዲያ ተቋማት፤ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፤ የክልል ቢሮዎች፤ የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋና ዋናዎቹ የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በሃገሪቱ በ2015 በጀት አመት ውስጥ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች የድረ ገጽ ጥቃት 2,554፤ ማልዌር 1‚295 ፤ የመሰረተ ልማት ቅኝት (Scan) 603 ፤ የመሰረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS) 1,493 ፤ ሰርጎ መግባት ሙከራ 695፤ እና ሌሎች የጥቃት አይነቶች 145 እንደየቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸዉ ናቸው፡፡

በተያያዘም የሳይበር ደህንነት አደጋ ዳሰሳ ከተደረገባቸዉ 123 (64 የመንግስት እና 59 የግል) ተቋማት የዌብ፣ የኔትዎርክ መሰረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን፣ አሰራር ስርዓት ጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች 652 የሳይበር ደህንነት የተጋላጭነት የአደጋ ደረጃ (Vulnerability risk level) ክፍተት መገኘቱን እና ከነዚህ ውስጥ 187 የሚሆኑት ከፍተኛ፣ 273 መካከለኛ እና 192 የሚሆኑት ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 4,336 የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎች ውስጥ 583 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት አደጋ ደረጃ ለማመላከት በተመረጡ ሦስት ዘርፎች (የሚድያ ተቋማት፣ የፀጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ቁልፍ መሰረት ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት) ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትን እና ተጋላጭነትን በማጣመር የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር በሃገር ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማዳን ችሏል፡፡

ከላይ በዝርዝር የቀረቡ የጥቃት ሙከራዎችን ተቋሙ ያከሸፈ ሲሆን ጥቃቶቹ ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ፣ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን እንደነብርና በዚህም ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችልን 23.2 ቢሊዮን ብር ከኪሳራ ማዳን መቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት የጋራ ሀላፊነት በመሆኑ ተቋማት የሳይበር ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ዋና ዋና የሳይበር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶችን ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከነዚህም መካከል ወቅቱ የሚጠይቀውን የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ ቴክኖሎጂን መታጠቅ፤ የሳይበር ደህንነትን ያማከለ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፤ ብቁ እና በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል አደረጃጀት ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ተከታታይ እና አቅምን ያገናዘበ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና እና አቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ወቅታዊና ተጨማሪ የሳይበር ደህንነት መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.insa.gov.et

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/INSA.ETHIOPIA

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/@cyberigna1003/featured

ቴሌግራም፦ https://t.me/insagovet

ትዊተር፦ https://twitter.com/INSAEthio

ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@insa.gov