በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተሰነዘሩ 3406 አደገኛ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከ96 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ማክሸፉን ኤጀንሲው ገለጸ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

 

አዲስ አበባ: ጥር 17/2014: ኤጀንሲዉ በ2014 በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዉስጥ ከ3400 በላይ 'አደገኛ' የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መከሰታቸዉን እና ከዚህ ውስጥ ከ96 ከመቶ በላይ ያህሉን ማክሸፉን ገልጿል።

ቀሪዎቹ ከ4 ከመቶ በታች የሚሆኑትን የጥቃት ሙከራዎች ደግሞ ምላሽ በመስጠት ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታዉቋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ 3,406 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መፈጸማቸዉን ጠቁመዋል፡፡

ካለፈው የ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዚህ በጀት አመት የተሞከረዉ የሳይበር ጥቃት ሶስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ጥቃቱ ከአመት ወደ አመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ለጥቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ዓለም አቀፍ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚነት ማደግ፣ በዘርፉ ወንጀልን ለተለያዩ ዓላማዎች የሚጠቀሙ ተዋኒያን መበራከት፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና የጂኦ-ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች መጨመር እንዲሁም ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ዶ/ር ሹመቴ ተናግረዋል፡፡

በስድስት ወራት ከተሞከሩ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹን ጥቃቶች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማክሸፍን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ ፣ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን ነበር ብለዋል።

አብዛኛዎቹ ጥቃቶች ትኩረታቸዉን በፋይናንስና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በመንግስት መ/ቤቶች ላይ ያነጣጠሩ እንደነበር ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች ዉስጥም የድረ-ገጽ ጥቃት ፣ የማልዌር ጥቃት እና የመሠረተ-ልማት ቅኝት ጥቃቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በተለያዩ ህገወጥ አካላት የተሰነዘሩ መሆናቸው የተናገሩት ዋ/ዳይሬክተሩ ጥቃቶቹ በተለይም ከህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ በሀገር ውስጥ ካሉ ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ካላቸው አካላት እና በሀገራችን ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን ማስገባት በሚፈልጉ ምእራባዊያን ጨምሮ ከተለያዩ የአለም ሀገራት በሚገኙ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች መሆኑን አብራርተዋል።

ኤጀንሲው በየጊዜው ባህሪውን የሚለዋውጠውን የሳይበር ደህንነት ዘርፍ ታሳቢ ያደረገ ሀገራዊ ፣ ቀጠናዊ እንዲሁም አለምአቀፍ የሳይበር ምህዳሩን ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማጥናት፣ ቀድሞ የመዘጋጀት፣ የማቀድና በጥብቅ ዲሲፕሊን ስራዎችን በመሰራቱ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ የሳይበር ጥቃትን የማስጠበቅና የመጠበቅ ቁመናው አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ሹመቴ ገልጸዋል፡፡

"የሳይበር ደህንነት የሁሉም ኃላፊነት ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማት ስነ-ምግባር የተላበሱ ሙያተኞችን እንዲኖራቸው በመሥራት፤የሳይበር ደህንነቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ፣ የሚጠቀሙባቸውን ሲስተሞች ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ኦዲት በማስደረግ እና የአሠራር ሥርዓቶችን በአግባቡ በመተግበር የሳይበር ደህንነት ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሹመቴ አሳስበዋል፡፡