2ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ዛሬ በይፋ መከበር ጀመረ!!

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

2ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር "የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት! እንወቅ! እንጠንቀቅ!" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሸራተኛ አዲስ በይፋ መከበር ጀምሯል፡፡

በመክፈቻ መርሃብሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ባስተላለፉት መልዕክት ዓለም በሳይበር ምህዳር ምክንያት አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን ስለ ሳይበር እና የሳይበር ደህንነት ምንነት፣ የዘርፉን ባህሪያት፣ አወንታዊና አሉታዊ ጎኖቹና ተጽዕኖዎቹን በአግባቡ ማወቅና መረዳት ከምንግዜዉም በላይ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የሳይበር ምህዳሩ እየፈጠረው በመጣው ከፍተኛ ተጽዕኖ ምክንያት የኃያላኑም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ መወዳደሪያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የሳይበር ምህዳር ሁሉን አቀፋዊ መሆን ለዓለማችን ይዞ የመጣውን አያሌ መልካም ዕድሎች የመያዙን ያክል በተቃራኒው ደግሞ ለሀገራት ሉዓላዊነትና ለህዝቦች ደህንነት የስጋት ምንጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈመ የበርካታ ሀገራት ሉዓላዊነት በሳይበር ምህዳሩ ውስጥ በውንብድና በተሰማሩ አካላት ሲነካባቸው፣ የተቋማትና የግለሰቦች ሀብት፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ሲበረበርና የአንዳንዶቹም እስከወዲያኛዉ ሃብታቸዉና ሚስጥራችው ሳይመለስላቸው ተወስደው ሲቀሩ መመልከት እየተለመደ መምጣቱን የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሹመቴ የጠቆሙት።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 የምናከብረውን ይህን ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ወር የዜጎችን እና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት አቅምን ለማጎልበት ሁላችንም የሚጠበቅብንን ለመወጣት እንደ መነሻ እንጠቀምበት ሲሉ ዶ/ር ሹመቴ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚንሰትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው በሀገራችን የበርካታ ዜጎችና ተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እንዲሁም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚያደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው ከዓመት ወደ ዓመት እያደጉ በመጡ ጥቃቶች 90 በመቶ ያህሉ የሚከሰሰቱት ከግንዛቤ ጉድለት ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ከሀገራችን ወቅታዊ የሳይበር ደህንነት ሁኔታ አንጻር የተለያዩ መንግስታዊ እና ህዝባዊ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ በመሆኑ ተጋላጭነቶችን ቀድሞ መመርምር የሚችል ብቁ ባለሙያ ማፍራት የሳይበር ደህንነት ስትራቴጂ ዋነኛ ምሶሶ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

ብቁ ባለሙያ ለማፍራትም ከምንወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ የሳይበር ደህንነት ትምህርትን ማስፋፋት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ፕሮፌሰር ብርሃኑ "እንደማህበረሰብ ሳይበርን መሠረት አድርገው ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች ያለብንን አነስተኛ የንቃተ ህሊና ደረጃ ለማሻሻል የሚመለከተቸው ተቋማት በተለይም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

በአለም አቀፍ እና ሀገራችን ስላለዉ የሳይበር ደህንነት ነባራዊ ሁኔታ ላይ በኢመደኤ የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ማዕከል ኃላፊ አቶ ፍፁም ወሰኔ ገለጻ ከተደረገ በኋላ ከተለያዩ ተቋማት በመጡ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች አማካኝነት የፓናል ዉይይት እየተካሄደ ይገኛል።