የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአማራ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለዉን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

[#if smallImage??]
  [#if smallImage?is_hash]
    [#if smallImage.alt??]
      ${smallImage.alt}
    [/#if]
  [/#if]
[/#if]

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2014: የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የአማራ ባንክ በሳይበር ደህንነትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬ እለት ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ አስተዳደሩ የሃገሪቱን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ስውሩን የሳይበር ጦርነት እየተዋጋ ነው ያሉት ፤ በዚህ ሂደትም የፋይናንስ ተቋማት ካላቸዉ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው ከባንኮች ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ባንክ ቴክኖሎጂ ለባንኮች እጅግ ወሳኝ ግብአት መሆኑን ተገንዝቦ እንዲሁም የተጋላጭነቱም መጠን ከፍተኛ መሆኑን ተረድቶ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ለመስራት ዝግጅነቱን ማሳየቱ የሚደነቅ ነዉ ብለዋል ።

ከዚህ ባለፈ ባንኩ በሰዉ ሃይል፣ በፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን እና ትብብሮችን ለማድረግ የሚያስችለዉን የዉል ስምምነት መፈረሙ ለሌሎች ባንኮችም በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር ነዉ ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

የአማራ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸዉ ባንካቸዉ የፋይናንስ ሰራዉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በርካታ ስራዎችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ደህንነት የሚያስፈልጋቸዉ ናቸዉ ብለዋል። በዚህ ረገድ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በኩል የምናገኘዉ ሙያዊ እገዛ ለባንኩ ስራ ስኬት አጋዥ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሳይበር ደህንነት አስተዳደር ዙሪያ ከባንኩ ጋር አብሮ ለመስራት ላሳየዉ ፍቃደኝነት እናመሰግናለን ያሉት ፕሬዝደንቱ ሌሎች ከአስተዳደሩ የሚገኙ የቴክኒክ እገዛዎች ለባንኩ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ ጠቁመዋል።

በስምምነቱ መሰረት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሳይበር ደህንነት አስተዳደር ፣ በአይሲቲ አገልግሎት የማማከር፣ የሳይበር ደህንነት ኦዲት ስራ የመስራት፣ በአይቲ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ ፣ በአይሲቲ አስተዳደር ፣ፖሊሲ ማልማት ፣ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ በሚዘጋጁ መመሪያዎች እና ደንቦች ላይ የማማከር ስራ የሚሰራ ሲሆን ከዚህ ባሻገር የቴክኒክ ስልጠናዎችን ለባንኩ የሚሰጥ ይሆናል።