አስተዳደሩ የሃገሪቱን የመረጃ ደህንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያላቸዉን ሶፍትዌሮችን እንዲያበለጽግ ኮሚቴዉ ጠየቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

 

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2014: የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /ኢመደአ/ አስተዳደሩ የሃገሪቱን የመረጃ ደህንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያላቸዉን ሶፍትዌሮችን እንዲያበለጽግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው ሰሞኑን በአስተዳደሩ ተገኝቶ የ9 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

ኢንፎርሜሽን በየትኛውም ዘርፍ ወሳኝ ግብዓት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተቋሙ የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሠረተ-ልማት ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የሚሠራቸውን ሶፍትዌሮችን የማልማት ሥራ ኮሚቴው በበጎ ጎኑ ተመልክቷል።

በሳይበር ዘርፍ ተሰጥዖ ያላቸው ተማሪዎች በተቋሙ ተገኝተው ባላቸው ተሰጥዖ መሠረት የተለያዩ ሶፍትዌሮችን እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል እና የሀገር ሉዓላዊነትን መጠበቅ የዚህ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።

ተቋሙ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ጠቁመው፣ በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን የሚደረጉ የጥቃት ሙከራዎች በተቋሙ መምከናቸውንም ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል ብለዋል።

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋሙ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን መቋቋም እንዲቻል በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ማበልጸግ መቻሉን ገልጸዋል።

ደህንነታቸው የተጠበቀ ምርት እና አገልግሎቶችን በከፊል እና በሙሉ ዓቅም በማበልጸግ እና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን የማረጋገጥ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሠረተ-ልማት ደህንነትን የማስጠበቅ ዓቅም በመገንባት፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ከማስጠበቅ ረገድ፣ ቁልፍ ተግባራት እንደተከናወኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ዘርፉ ተለዋዋጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በታሰበው ፍጥነት መጓዝ እንዲቻል የሳይበር ደኅንነት የሕግ ማዕቀፎች እና የጥራት ደረጃዎች እንዲወጡ እና በፍጥነት እንዲጸድቁም፣ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግላቸው ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ጠይቀዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የ2014 በጀት አመት የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበ ሲሆን፤ ከሪፖርቱ በተጨማሪም በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱም በአስተዳደሩ ዋና መ/ቤት በመገኘት የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡