ኢመደአ የራሱን የህክምና ማዕከል አስመረቀ

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የራሱን የህክምና ማዕከል አስመረቀ፡፡ የህክምና ማዕከሉን በይፋ የመረቁት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት የህክምና ማዕከሉ የጤና አገልግሎትን ለሠራተኛው ተደራሽ በማድረግ ጤናማና ምርታማ ሰራተኛ እንዲኖር በማገዝ የአስተዳደሩን ራዕይና ተልእኮ ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የህክምና ማዕከሉ በኢመደአ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ለሚገኙ አራቱም ተቋማት (የሰላም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ እና የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት) አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

ኢመደአ የሰራተኞቹን ጤና ለማስጠበቅ ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሰራተኞችን የህክምና ወጭ በአገር ውስጥ 100% (መቶ ኘርሰንት) ሽፋን በመስጠት በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ ሆኖም እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት የጊዜ ብክነት በመፍጠር በሥራ ሰአት ላይ ጫናን ሲፈጥር መቆየቱን ጠቁመዋል። ከዚህ አኳያ የህክምና ማዕከሉ የአስተዳደሩ አባላት የጤና ሁኔታቸውን በቅርበት ለመከታተልና ከአላስፈላጊ እንግልት የሚጠብቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢመደአ የሥራ ባሕሪ ረጅም ሠዓት መስራትንና ለተለያዩ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች የማጋለጥ ባህሪይ ያለው መሆኑን ያመላከቱት ዋና ዳሬክተሯ፤ በዚህ ረገድ የህክምና ማዕከሉ ለሰራተኛው ተደራሽና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በዚህም ሰራተኛው ስለጤናው ሁኔታ ሳያስብ በተረጋጋ ሁኔታ ሥራውን እንዲሰራ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ለህክምና ማዕከሉ በዚህ ደረጃ ተገንብቶ ለምርቃት መብቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን የውዳሴ እና ቤተሰቧ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ኤም.ኤስ.አይ ሪፕሮዳክቲቭ ቾይስና ሌሎችንም የውጭና የውስጥ አካላት ዋና ዳይሬክተሯ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ሃይረዲን ተዘራ በበኩላቸው፤ ሚንስትር መስሪያ ቤታቸው ማህበረሰባዊ ጤና ላይ በሚያተኩረው የሰላም ግንባታ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጤና ላይ መስራትም ለማህበረሰቡ አጠቃላይ ሰላምና ደህንነት ያለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ በኢመደአ የተገነባው የሕክምና ማዕከል አጠቃላይ ለሰራተኛው ሰላምና ደህንነት ተጨማሪ ዋጋ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ በቀጣይ ሚንስትር መስሪያ ቤታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የህክምና ማዕከሉ በግቢው ውስጥ ላሉት ለሁሉም ሰራተኞች አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የህክምና ማዕከሉን ወደ ሆስፒታል ደረጃ በማሳደግ የሰራተኛውን የጤና አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሃሚድ መሃመድ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሕክምና ማዕከሉ መገንባት ለሰራተኛው ዘላቂ ጤና መጠበቅ ጉልህ ሚናን እንደሚጫወት ገልጸው፤ በቀጣይ ለህክምና ማዕከሉ የሚያስፈልጉ እገዛዎችን ለማድረግ ተቋማቸው ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡

ለኢመደአ የህክምና ማዕከል ግንባታ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የውዳሴ እና ቤተሰቧ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ቤተልሔም እንቁ በበኩላቸው፤ በጤናው ዘርፍ ተባብሮ የመሥራት የድርጅታቸው ዋና መርህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢመደአ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ ጀምሮ የቆየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ግንኙነት በቀጣይም በላቀ ደረጃ በማሳደግ ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

ሌላዉ በህክምና ማዕከሉ ግንባታ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው አጋር አካላት መካከል አንዱ የሆነው የኤም.ኤስ.አይ ሪፕሮዳክቲቭ ቾይስ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ በበኩላቸው፤ በኢመደአ የተገነባው የህክምና ማዕከል ለሰራተኞቹ የህክምናና የጤና አገልግሎትን በአግባቡ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ትርጉሙ ትልቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ የህክምና ማዕከሉ የጤናና የህክምና አገልግሎት መስጫ ብቻ ሳይሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለሰራተኞቹ ምን ያህል ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን ማሳያ ምልክት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የህክምና ማዕከል የላብራቶሪ አገልግሎት፣ ቀላል የቀዶ ጥገና አገልግሎት፣ የህክምና ማማከር አገልግሎት፣ የድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚያስችለው መልኩ የተደራጀ ነው፡፡

Asset Publisher


የቅርብ ዜናዎች