የኖረ ሕልማዊ እንቆቅልሽ ተፈታ፤ የዛሬ የመቻል እውነታችን ተገለጠ፤ የነገ ትውልድ ተስፋ በአብርኾት ፈነጠቀ! ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!
የኖረ ሕልማዊ እንቆቅልሽ ተፈታ፤ የዛሬ የመቻል እውነታችን ተገለጠ፤ የነገ ትውልድ ተስፋ በአብርኾት ፈነጠቀ! ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላ ኢትዮጵያዊያን የደምና የላብ ጠብታ አሻራ ያረፈበት፤ በኢትዮጵያዊያን መሰናሰል እና መደመር ዕውን ያደረገ የአንድነታችን ሐውልት፤ የጥንካሬያችን ማሳያ ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከግድብም በላይ የሆነ፤ የትላንት ሕልማዊ እንቆቅልሽን የፈታ፤ የዛሬ እውነታችንን የገለጠ፤ የነገ ተስፋን የፈነጠቀ የሕያው ተጋድሎ ዳግማዊ አድዋችን ነው፡፡
ላለፉት ሰባት አመታት ሀገራችንን ወደ ተጨባጭ ብልጽግና እያደረሰ ያለዉ መንግስታችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ በሆነዉ የሕዳሴ ግድብ ላይ የወሰደው የእርምት እርምጃ ግድቡ ነብስ ዘርቶ፤ ለእኛ ኢትዮጵያውያን የእድገት ጉዞ አቅጣጫ ቀያሪ ምልክት እና የተስፋና የአብርኾት ዘመን ስንቅ ሆኖ የተገለጠ ገቢር ነበብ (Pragmatic) ስጦታችን እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ህልማችንን ለማጨናገፍ የዉስጥ ባንዳዎችና ከዉጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በከፍተኛ ደረጃ ሴራ በመጎንጎን ወደር የለሽ ጫናዎችን ፈጥረዋል። ከችግሮች በላይ መሆንን በውል የተረዳው መንግስታችን እና ህዝባችን የኢትዮጵያን ሀቅ በዓለም አደባባይ በማሳየት፤ ወጥ አቋም በመያዝ፤ የላቁ መንግስታዊ ውሳኔዎችንና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በማከናወን ዛሬ ከችግሮች በላይ ከፍ ብለን ድላችንን በዓለም አደባባይ ለማብሰር በቅተናል።
ውስጣዊ ህብረታችን እና ጥንካሬያችን በትናንት የአድዋ ታሪካችን እንዳየነው ሁሉ፤ ዛሬም የእሱ አምሳል ግብር የሆነው ህዳሴ ግድባችን ከእናቶቻችን መቀነት ተፈትቶ የተገደበ የአንድነታችን ማሳያ፣ የመለያየትን መስመር ያደበዘዘ የማንሰራሪያ ምልክታችን ሆኗል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገራችንን ብሎም የቀጠናውን የጂኦ-ፓለቲካ የሚቀይር፤ ከኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና የሚያሻግረን የዘመን ድልድያችን ነው፡፡
ግድቡ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሳትጠቀም ለሺህ አመታት የኖረችበትን የድህነት እና የኋላ ቀርነት ቀንበር የሰበረ፤ ወደፊት እየተጓዝንበት ያለውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን የዘመናት የድህነት ቀንበር መቋጫ ነው፡፡
ዛሬ የሀገራችን ማንሰራራት በሕዳሴ ግድብ ተበስሯል! ይህ ብስራት ከትውልድ እስከ ትውልድ እየተስተጋባ ይኖራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማንሻገረው ገደል፤ የማንወጣው ተራራ እንደሌለ ለዓለም አሳይተናል።
የእኛ የኢትዮጵያውያን የጥናካሬያችን ምንጭ አንድነታችን ነው! አንድነታችንን ከጠበቅን በላብና በደማችን የሀገራችንን ትንሳኤ አብስረን ለልጅ ልጆቻችን የበለጸገች፣ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ በዓለም አደባባይ በኩራት የምትታይ ኢትዮጵያን እናስረክባለን፡፡ በድጋሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!
ትዕግስት ሃሚድ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር