የዲጂታል ትግበራዎችን ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ
የዲጂታል ትግበራዎችን ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ
"ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ" በሚል መሪ ቃል የነገዉ ቀን በሳይንስ ሙዚየም የተከበረ ሲሆን በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዲጂታል ትግበራዎችን ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል ምህዳሩን በማስፋት የዘርፉን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ያነሱት ክቡር ሚንስትሩ የዲጂታል ትግበራዎችን ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ትናንት የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድ ዘመን ታላቅ ለውጥ ማሳያ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር በለጠ ለቤት፣ ለኢንዱስትሪ የኤሌትሪክ ኃይል እንደሚያቀርብ ሁሉ፤ ቴክኖሎጂን እና ኢኖቬሽንን የሚያለመልም መሆኑን ጠቁመዋል።
በዲጂታል የጎለበተች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች እና ለችግሮች የማትበገር ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት እንደሚገባም በመድረኩ አንስተዋል።
የነገዉ ቀን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጨምሮ በሰባት ተቋማት የተዘጋጀ የጷጉሜን ፕሮግራም ሲሆን በሁነቱ ላይ ኤግዚቢሽ፣ የፓናል ዉይይቶችና የሃካቶን ዉድድር ተከናዉኗል።