የጥንቃቄ መልዕክት
የጥንቃቄ መልዕክት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የቴሌግራም #TELEGRAM ና ዋትሳፕ #WhatsApp ተጠቃሚዎችን ያነጣጠረ የማጭበርበርና የአካዉንት ነጠቃ እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ መጥተዋል።
ከሰሞኑም ከዚህ ቀደም ከነበረዉ በተለየ ሁኔታ የግለሰቦች የቴሊግራምና ዋትሳፕ አካዉንቶችን በመረጃ መንታፊዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተነጠቀና ማጭበርበሮች እየተፈጸሙ መሆኑን በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር #INSA የሳይበር አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ መስጫ ማዕከል/Ethio-CERRT/ ማረጋገጥ ችሏል።
እነዚህ የአካዉንት ነጠቃዎች የሚፈጸሙት ለጥቃት ኢላማ ላደረጉት አካል አጥፊ ተልዕኮ ያላቸዉን ሊንኮችን#links በመላክና ሊንኩን እንዲከፍቱ የሚያደርጉ ቴክኒኮችን በመጠቀም ነዉ። ከእነዚህ ቴክኒኮች መካከል በጣም ወሳኝ በሆነ ጉዳይ አስቸኳይ በዙም ወይም በሌሎች የኦንላይን ፕላትፎርሞች ስብሰባ ስለሚኖር በተላከዉ ሊንክ አማካኝነት እንዲሳተፉ በመደወልና በማግባባት ሲሆን ሊንኩን ከፍተዉ በሚገቡበት ወቅት አካዉንታቸዉን ይነጥቃሉ።
ከዚህ የአካዉንት ነጠቃ በኋላ የተነጠቀዉን የቴሊግራም ወይም ዋትሳፕ አካዉንት በመጠቀም ወደ ግለሰቡ ወዳጆች ለወሳኝ ጉዳይ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸዉና እንዲያስገቡላቸዉ በጽሁፍ መልዕክት በመጠየቅ እያጭበረበሩ ይገኛሉ።
በመሆኑም የቴሌግራምና ዋትሳፕ ተጠቃሚዎች ከማታዉቁት አካል የሚላክላችሁን አጓጊ የሆኑና አስቸኳይነት ያላቸዉ ሊንኮች ሲላክልዎት እንዲሁም ሊንኩን እንዲከፍቱ ጥሪ ሲደርስዎት አካዉንትዎን ለመጥለፍ ሊሆን ስለሚችሉ ሊንኮችን ከመክፈት መቆጠብና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድታደርጉ #INSA ያሳዉቃል።
ከዚህ ባሻገር የቴሌግራምና የዋትሳፕ ተጠቃሚዎች ከወዳጅ ዘመድዎ ወይም የስራ ባልደረባዎ በእነዚህ አካዉንቶች የሚቀርብላችሁን የብድርና የድጋፍ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠትዎ በፊት ወደ ጠያቂዉ ስልክ ደዉለዉ ሳያረጋግጡ ማንኛዉንም ገንዘብ እንዳይልኩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ያሳስባል።