የድሮን ቴክኖሎጂ የግብርና ሥራን በማዘመን የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል
የድሮን ቴክኖሎጂ የግብርና ሥራን በማዘመን የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል
የድሮን ቴክኖሎጂ (Drone Technology) የግብርና ሥራን በማዘመን የሐገራችንን የምግብ አቅርቦትና ዋስትና ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ተገለጸ፡፡ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (Food and Agricultural Organization - FAO) ባዘጋጀው የድሮን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ስልጠና ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ኢትዮ ሬድ ፎክስ ከተባለ ካምፓኒ ጋር በጋራ በመሆን የድሮን ኦፕሬሽን ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ለአራት ቀናት በቆየው ስልጠና የድሮን ቴክኖሎጂ ለግብርና እና ለውሃ ሃብት አስተዳደር ያለውን ሚና በተመለከተ ተግባር ተኮር ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ በስልጠናው ላይ ከሊቢያ እና ከሞዛምቢክ እንዲሁም ከሐገራችን ከተለያዩ የግልና የመግስት ተቋማት እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በድሮን ቴክኖሎጂ ኦፕሬሽን ያለውን ልምድና ተሞክሮ ለስልጠናው ተሳታፊዎች ያካፈለ ሲሆን በቀጣይ ከቀጠናው እንዲሁም ከአፍሪካ ሐገራት ጋር በጋራ በመሆን የድሮን ቴክኖሎጂን ለግብርና ሥራ በስፋት በማዋል የምግብ አቅርቦትና ዋስትናን ለማረጋገጥ በጥምረት እንደሚሰራ ተገለጿል፡፡
የድሮን ቴክኖሎጂ በአለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በሐገራችን አዲስ ቴክኖሎጂ ከመሆኑ አኳያ የቴክኖሎጂውን ምንነትና አጠቃቀም እንዲሁም ቴክኖሎጂውን ለማስተዳደር የሚያገለግሉ የሕግ ማዕቀፎች ምን እንደሚመስሉ በስልጠናው ላይ በስፋት ተዳሷል፡፡ ከስልጠናውም ባሻገር በተግባር የታገዘ የድሮን በረራ፣ ዳታ መሰብሰብ እና የተሰበሰበውን ዳታ የመተንተንና ጥቅም ላይ የማዋል የመስክ ተግባርም ለስልጠናው ተሳታፊዎች ተሰጥቷል፡፡